19 ህፃናት በተገደሉበት የቴክሳስ ጥቃት ፖሊስ መጀመሪያ የሰጠውን መረጃ መቀየሩ ቁጣን ፈጠረ

በጥቃቱ ቤተሰብ ያጡ ሃዘንተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ 19 ህፃናትና ሁለት መምህራን የተገደሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ፖሊስ መጀመሪያ የሰጠውን መረጃ መቀየሩ ቁጣን ፈጥሯል።

ፖሊስ መረጃውን ያሻሻለው ለጥቃቱ የተሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ከበርካታ ቤተሰቦች ከፍተኛ ትችት መሰማቱን ተከትሎ ነው።

ታጣቂው ወደ ኡቫልዴ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት ለ12 ደቂቃ ያህል ከግቢው በር ሲዟዟር እንደነበርና ማንም ያስቆመው እንደሌለም ፖሊስ በተሻሻለው መግለጫው አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም ፖሊስ ከሰጠው ታጣቂው ወደ ትምህርት ቤት ሊገባ ሲል ከአንድ ፖሊስ ጋር በነበረው ፍጥጫ በጥይት ተመትቷል ከሚለውም ጋር ይቃረናል።

ታጣቂው ደርሶ ከ90 ደቂቃ በኋላ በጥይት ተመትቶ ከመሞቱ በፊት 19 ህጻናትን እና ሁለት መምህራንን ገድሏል ሲል ፖሊስ ተናግሯል።

የፖሊስ መዘግየትና ታጣቂው ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ ወላጆች መሬት እንዲተኙ ሲደረግና ሲታሰሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ጋር ተዳምሮ የአሜሪካውያን ቁጣ እንዲጨምር እንዲሁም ምላሽ አሰጣጡ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አጭሯል።

በተጨማሪም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የከተማዋ አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት ታጣቂው ወደ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት ደፋር መኮንኖች ፈጣን የሆነ ምላሽ በመስጠት ከልክለውት ነበር ማለታቸው ከፍተኛ ጥያቄ አስነስቷል።

አስተዳዳሪው "የፖሊስ መኮንኖቻችን ወደ ታጣቂው በመሮጥ አስደናቂ ድፍረት አሳይተዋል" ብለዋል።

በተጨማሪም በቴክሳስ የፖሊስ መኮንን ቪክተር ኢስካሎን ቀደም ሲል የሰጧቸውን መግለጫዎች ማስተካከል እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ፖሊስ የሰጠውን ምላሽ በመደገፍና ታጣቂው ያደረሰው ተኩስም በመኮንኖቹ ላይ ያደረሰውን የመንፈስ መሰበርም አስረድተዋል። "ሁላችንም ውስጣችን እንደተጎዳ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን በዛሬው ዕለት፣ ሐሙስ ከተሰጠው መግለጫም በኋላ ቢሆን ሁኔታዎች የተከሰቱበት ዝርዝር ሁኔታ ግልፅ አይደለም።

የፖሊስ መኮንኖች ትምህርት ቤቱ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀባቸው እንዲሁም የ18 አመቱ ታጣቂ ሳልቫዶር ራሞስ ከመገደሉ በፊት ከአንድ ሰዓት በላይ ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንዴት ቆየ የሚለውም ጥያቄ መልስ አላገኘም ።

ታጣቂው የተገደለው በአካባቢው ፖሊሶች ሳይሆን በአሜሪካ የድንበር ወኪሎች በሚመራ የታክቲክ ክፍል መሆኑም ሌላ ጥያቄ አጭሯል።