ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ ካሊፋ በ73 አመታቸው አረፉ
በአለም ላይ ካሉት ከናጠጡ ንጉሶች አንዱ የሆኑት የየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በ73 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ የተባባሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት የሆኑት ሼክ ካሊፋ በአውሮፓውያኑ 2014 በስትሮክ ህመም በመጠቃታቸው ከመንግሥት ስራዎች ገለል ብለው ነበር።
ወንድማቸው ሞሃመድ ቢን ዘይድ አል-ናህያን በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ጉዳዮች ሃላፊ ናቸው።
የአል-ናህያን ቤተሰብ 150 ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንዳላቸው ይታመናል።
ሼክ ካሊፋ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሰባቱ ኤምሬት መዲናና በነዳጅ የበለፀገችው አቡ ዳቢ ገዥ ነበሩ።
የሞታቸው ዜና ይፋ የሆነው በደብልዩ ኤም የዜና ወኪል ነው።
የፕሬዝዳንት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከዛሬ ዓርብ ጀምሮ ለ40 ቀናት የሐዘን ቀናትን ያወጀ ሲሆን በዚህም ወቅት ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ እንዲሁም በመንግሥትም ሆነ በግል ዘርፍ ስራ ለሶስት ቀናት ታግዷል።
ሼክ ካሊፋ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሁለተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው በአውሮፓውያኑ 2004 ከአባታቸው ስልጣን የተረከቡ ሲሆን የአቡ ዳቢ 16ኛ ገዥ ነበሩ።
በስልጣን ዘመናቸው በመጀመሪያዎቹ አስርት አመታት የፌደራል መንግስቱንም ሆነ የአቡዳቢን የመንግሥት መዋቅር በመለዋወጥ ትልቅ ሰራ ሰርተዋል።
ነገር ግን በስትሮክ ህመም ከታመሙ በኋላ ውሳኔዎችን ቢያስተላፉም በአደባባይ ብዙም አይታዩም ነበር።