ኬንያዊያን መምህራን "ተማሪዎችን መግረፍ ይፈቀድልን" ሲሉ ጠየቁ

ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በኬንያ ሕግ ተማሪ መግረፍ ቅጣት ያስከትላል።

ኬንያ፤ ተማሪዎች ላይ አካላዊ ጉዳት የሚያስከትል ቅጣት የከለከለችው በፈረንጆቹ 2001 ነው።

ነገር ግን ከቅብር ጊዜያት ወዲህ የተወሰኑ ኬንያዊያን መምህራን "ተማሪዎቻችን መግረፍ ይፈቀድልን" ሲሉ እየጠየቁ ነው።

መምህራኑ ይህን ጥያቄ የሚያቀርቡት ተማሪዎችን "ሥርዓት ለማስያዝ" እንደሆነ ይናገራሉ።

ቺልድረንስ አክት የተባለው የኬንያ ሕግ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ተማሪዎች ላይ እንዳይደርስ ያግዳል።

ቢሆንም የአንዳንድ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ተማሪዎች ልቅ እንዳይሆኑ ማድረግ እንሻለን ይላሉ።

"ሕፃናትን ማስተዳደር ትልቅ ልፋት ይጠይቃል" የሚለው የኬንያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት አስተዳዳሪዎች ማሕበር ኃላፊ ነው።

ካሂ ኢንዲሙሊ እንደሚለው ሕጉ "አስተማሪዎች የትኛውንም ዓይነት የዲሲፕሊን እርምጃ እንዳይወስዱ ያግዳል" ይላል።

የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች በዚህ ሳምንት ስብሰባ ለማድረግ አቅደዋል።

የስብሰባው ዋና አጀንዳ በትምህርት ቤቶች እየጎላ የመጣውን ቀውስ እንዴት ማስታገስ ይቻላል የሚለው ነው።

በኬንያ ትምህርት ቤቶች ተቃጠሉ የሚለው ዜና አዲስ አይደለም።

ብዙውን ጊዜ እሳት ለኩሰው መማሪያ ክፍላቸውን ዶግ አመድ የሚያደርጉት ደግሞ ተማሪዎች ነው።

በተለይ ደግሞ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች 'የሚቀርብልን ምግብ አልተስማማንም' አሊያም 'አስተማሪዎች በድለውናል' በማለት እሣት ይለኩሳሉ።

ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በቀሰቀሱት እሣት ተቃጥለዋል።

ባለፈው የካቲት የትምህርት ሚኒስትሩ ጆርጅ ማጎሃ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን መግረፍ እንዳያስቡት አስጠንቅቀዋል።

ነገር ግን ሚኒስትሩ ዲሲፕሊን ማስያዝን በተመለከተ የፖሊሲ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከሁለት ወራት በፊት አንዲት ተማሪ ትምህርት ቤቷን አቃጥላ ጥፋት በማድረሷ የአምስት ዓመት እሥር ተጥሎባታል።

የ18 ዓመቷ ተማሪ የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለች ሞይ የተሰኘውን የሴቶች ትምህርት ቤት አቃጥላ ለ10 ተማሪዎች ሞት ምክንያት ሆናለች።