ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥቃቶችን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር “የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የመውሰድ ነጻነት ይኖራቸዋል” አሉ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በቴል አቪቭ አንድ ፍልስጤማዊ በፈጸመው ጥቃት ሦስት እስራኤላውያንን መገደላቸውን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የመውሰድ "ሙሉ ነፃነት" አላቸው አሉ።
ሐሙስ ምሽት አንድ ፍልስጤማዊ በቴል አቪቭ በሚገኝ መጠጥ ቤት ላይ ተኩስ ከፍቶ ሁለት ሰዎችን ወዲያው ሲገድል ሦስተኛው አርብ ዕለት ሕይወቱ አልፏል።
ጥቃት አድራሹ በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደበት እርምጃ ከመገደሉ በፊት ለአራት ሰዓታት ሲታደን ነበር።
በእስራኤል በቅርብ ጊዜ ውስጥ በደረሱ ተከታታይ ጥቃቶች 14 ሰዎች ተገድለዋል።
የ28 ዓመቱ ራድ ሃዜም ከጄኒን በቴል አቪቭ እምብርት ውስጥ በሚኝ በሰዎች በተሞላ ባር እና ሬስቶራንት ውስጥ ተኩስ ከፍቶ ተሰውሮ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ከ1 ሺህ የሚልቁ የእስራኤል ፖሊስ አባላት፣ ልዩ ኃይል እና የስለላ አገልግሎት አባላት ተሰማርተው ራድ ሃዚም ሲታደን የነበረ ሲሆን ነዋሪዎችም ቤታቸው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር።
ከሰዓታት ፍለጋ በኋላም ሀዚም ጥቃቱን ከፈጸመበት ሥፍራ አራት ማይል ርቀት ላይ በሚገኝ መስጊድ አቅራቢያ ተደብቆ የተገኘ ሲሆን ከፀረ-ሽብርተኝነት እና ከደህንነት አባላት በተከፈተ ተኩስ ተገድሏል።
አርብ ማለዳ ላይ በቴል አቪቭ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት የጸጥታ ኃይሎች የደህንነት ስጋትን ለመመከት ነጻነት ይኖራቸዋል ብለዋል።
"ለዚህ ውጊያ ገደቦች የሉም፤ አይኖሩምም። ሽብርተኝነትን ለማሸነፍ ለጦር ኃይሉ፣ ለአገር ውስጥ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲሁም ለሁሉም የጸጥታ ኃይሎች ሙሉ ነጻነትን እያረጋገጥን ነው። እያንዳንዱን ነፍሰ ገዳይ አድነን እንደምንይዘው ያውቃል። አሸባሪን የሚረዳ ሁሉ ከባድ ዋጋ እንደሚከፍል ማወቅ አለበት" ብለዋል።
የሐሙስ ዕለት ጥቃቱን ያደረሰው ፍልስጤማዊ ግለሰብ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ እስራኤል እንደገባ የተረጋገጠ ቢሆንም ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ያለው ግንኙነት ግን አልታወቀም።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ሰላማዊ ሰዎችን መግደል የተገባ አይደለም በሚል ድርጊቱን አውግዘውታል። "የሲቪል ፍልስጤም እና እስራኤውያን መገደል ነገሩን የበለጠ ያበላሸዋል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሆኖም የጋዛ ሰርጥን የሚቆጣጠረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ እና የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ጥቃቱን 'ተገቢ ነው' ሲሉ አድንቀናል ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ዋሽንግተን ጥቃት እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ከእስራኤል ጎን በቁርጠኝበት እንደምትቆም ተናግረዋል።
የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በቅርብ እየተበራከቱ የመጡ ጥቃቶችን ተከትሎ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ በቴል አቪቭ የአይሁድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ተቋም አካባቢ አምስት ሰዎች በአንድ ፍልስጤማዊ ታጣቂ በተከፈተባቸው ተኩስ ተገድለዋል።
ከቀናት በፊት ደግሞ ሰሜን ሃደራ ከተማ እና በቤርሳቤህ ደቡባዊ ከተማ ሦስት የአረብ የዘር ሐረግ ባላቸው እስራኤላውያን በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች 6 ሰዎች ተገድለዋል። ከክስተቱ በኋላ ጥቃት አድራሾቹ በተከፈተባቸው ጥቃት ተገድለዋል።