የደቡብ አፍሪካው የፀረ ስደተኞች ቡድን መሪ ከእስር በዋስ ተለቀቀ

ንህላንግላ ለክስ ድላሚኒ ፍርድ ቤት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ንህላንግላ ለክስ ድላሚኒ ፍርድ ቤት ውስጥ
ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ የፀረ ስደተኞች ቡድን መሪ የሆነው ንህላንግላ ለክስ ድላሚኒ ለጥቂት ቀናት ጆሃንስበርግ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከቆየ በኋላ በዋስ ተለቀቀ።

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞች ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ የሚጠይቀው 'ዱዱላ' የተባለው ቡድን መሪ ሲሆን፣ የቡድኑ እንቅስቃሴ በርካታ ስደተኞችን ስጋት ላይ ጥሏል።

የ33 ዓመቱ ድላሚኒ ለክስ ከአርብ ጀምሮ ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በእስር ከቆየ በኋላ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ በዝርፊያ፣ በስርቆትና ንብረት የማውደም ክስ ቀርቦበታል።

ችሎቱም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ተጠርጣሪው በ1,500 ራንድ (የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ) ወይም በ100 ዶላር ዋስትና እንዲለቀቅ ፈቅዷል።

ድላሚኒ ላይ ለእስር የበቃው አንድ የሶዌቶ ነዋሪ በግለሰቡ የሚመራው 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የተባለው ቡድን አባላት ወደ ቤቱ ገብተው ንብረት አውድመዋል በሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ ነው።

ሶዌቶ ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት መኖሪያ ቤቱ ላይ ጥቃት የደረሰበት ግለሰብ በቤቱ ውስጥ ዕጽ ይሸጣል በሚል የቡድኑ አባላት ሊያናግሩት ሄደው ነበር ብለዋል።

የዱዱላ ቡድን መሪው ንህላንግላ ለክስ ድላሚኒ ጠበቆች በደንበኛቸው ላይ የቀረበው ክስ እዚህ ግባ የማይባል ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

በግለሰቡ የሚመራው ቡድን 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የመኖሪያና የመሥሪያ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ከአገሪቱ እንዲወጡ ዘመቻ ያካሂዳል። በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እንደሚዋጋና ወንጀለኞችን እንደሚያሳድስ ይናገራል።

ብዙም የማይታወቅ የነበረው ይህ ቡድን በአገሪቱ ውስጥ መገለል ገጥሞናል በሚሉ በአንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰቦች ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ ሲሆን፣ ቡድኑ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በአገሪቱ ከዚህ በፊት እንደተከሰቱት አይነት መጤ ጠል ጥቃቶችን እንዳይቀሰቅስ ተሰግቷል።

ንህላንህላ ለክስ ድላሚኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ንህላንህላ ለክስ ድላሚኒ

ኦፕሬሽን ዱዱላምንድን ነው?

የኦፕሬሸን ዱዱላ መቀመጫ በጆሃንስበርግ ሶዌቶ ነው።

በ33 ዓመቱ ንህላንህላ ለክስ ድላሚኒ የተመሰረተ ሲሆን የበለጠ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሶዌቶ ነዋሪዎች ስደተኞችን "ጠራርገን እናስወጣቸው" የሚል ዘመቻ በጀመሩበት ወቅት ነበር።

ይህ ዘመቻ ትኩረት አድርጎ የነበረው የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን እና በሕገወጥ የመንግሥት ንብረቶችን ይዘዋል ባሏቸው ግለሰቦች ላይ ነበር።

ነገር ግን በአሌክሳንድራ ብቻ የቡድኑ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ እየሰፋ መጥቷል።

የዚህ ቡድን አባላት አሁን በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በውጪ አገራት ዜጎች የተያዙ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አነስተኛ ንግዶች ደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ቀጥረው እንዲያሰሩ ፍላጎት አላቸው።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ደቡብ አፍሪካውያንን ገሸሽ አድርገው በዝቅተኛ ዋጋ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ይቀጥራሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ባለስልጣናት እንደዚህ አይነት አዝማሚያዎች ቢኖሩም ይህ ግን የተስፋፋ አለመሆኑን ይናገራሉ።

የቡድኑ አባለት መጤ ጠል አይደለንም ሲሉ ይናገራሉ። አክለውም የደቡብ አፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከአደጋ እየተከላከሉ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚያም ወደ ኤኤንሲ፣ ገዢው ፓርቲ፣ ጣታቸውን በመቀሰር ይህንን ማድረግ ተስኖታል ሲሉ ይወነጅሉታል።

አባለቱ አክለውም ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ይገልጻሉ።