ታሊባን የሴቶችን ትምህርት ቤቶች እንዲከፍት የሚጠይቅ ሰልፍ ተካሄደ

በአብዛኛው ሴቶች የተሳተፉበትና ታሊባን የሴቶችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲከፍት የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።
ሰላማዊ ሰልፉ የተካሄደው ቅዳሜ ጠዋት የአፍጋኒስታን ትምህርት ሚኒስቴር አቅራቢያ ነው።
ታሊባን ባለፈው ሳምንት መባቻ ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ ውሳኔ ማስተላለፉ እያስወቀሰው ይገኛል።
በአዲሱን የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ቀን ነበር ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ የተወሰነው።
"መማር መብታችን ነው! የሴቶችን ትምህርት ቤቶች ክፈቱ!" የሚል መፈክር ሰልፈኞቹ አሰምተዋል። ይህንን ሲሉ በአቅራቢያቸው ታጣቂ የታሊባን ወታደሮች ነበሩ።
በሰልፉ ላይ የተገኘች አንዲት መምህርት ለቢቢሲ "ለነጻነት እንዲሁም መማር የሚፈልጉ ሴቶች ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ስታገል ብሞት እንኳን አይቆጨኝም" ብላለች።
"ለልጆቻችን የመማር መብት ለመታገል ነው ሰልፍ የወጣነው። ይህ መብት ካልተከበረ እንደሞትን ብንቆጠር ይሻለናል" ስትልም አክላለች።
ከዚህ ቀደም ታሊባን ሰልፎችን በትኖ ተሳታፊዎችን አስሯል። ይህኛው ሰልፍ ሲካሄድ ግን ታሊባን ለማስቆም አልሞከረም።
ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ ወዲህ የመጀመሪያ ደረጃ የወንዶች እና ሴቶች ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥሉ ቢደረግም፣ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይገቡ ታግደዋል።
የታሊባን የትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይጀመራል ቢልም ውሳኔው በታሊባን ማዕከላዊ አመራር ኮሚቴ ተሽሯል።
ኮሚቴው ለትምህርት ቤቶቹ "ጥልቅ እስላማዊ ዕቅድ እስከሚወጣ" ዝግ እንደሚሆኑ ገልጿል።
ይህ ውሳኔ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣ ቀስቅሷል።
በአዲሱ የትምህርት ዓመት፣ በመጀመሪያው ቀን ትምህርት ለመከታተል ከቤታቸው ከወጡ በኋላ ትምህርት ቤታቸው እንደተዘጋ የሰሙ አፍጋኒስታናውያን ሴት ታዳጊዎች ሲያለቅሱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተለቀዋል።
'ቶሎ' የተባለ ታዋቂ የቴሌቭዥን ጣቢያ አቅራቢ ስለ ጉዳዩ ውይይት ሲመራ እንባ እየተናነቀው ነበር።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንደምን ጨምሮ የ10 አገራት አመራሮች የታሊባን ውሳኔ "እጅግ የሚረብሽ ነው" ብለው ኮንነውታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታሊባን ጋር ኳታር ውስጥ ሊያካሂድ የነበረውን ውይይት ሰርዟል።
ታሊባን ከዚህ በፊት የሴቶች ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ወስኖ አሁን ደግሞ ውሳኔውን መቀልበሱ በቡድኑ ውስጥ በአክራሪዎች እና ተራማጆች መከፋፈል እንዳለ ይጠቁማል።
በአንዳንድ ሰሜናዊ የአፍጋኒስታን አካባቢዎች ሴት ታዳጊዎች ትምህርት እንዲቀጥሉ ሲፈቀድ በሌሎች አካባቢዎች ግን አመራሮች ከልክለዋል።
ሰልፍ ከወጡት አንዷ በቁጣ እያለቀሰች "ትውልዳችን ነጻ ሆኖ እንዲያድግ እሻለሁ። በየቤታችን ተቀምጠን ማልቀስ የለብንም" ብላለች።

















