በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሳምንት ውስጥ በ1 ሚሊዮን አሻቀበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ በአንድ ሚሊዮን መጨመሩን የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ አመለከተ።
በከፍተኛ ፍጥነት በሚዛመተው ኦሚክሮን ቢኤ 2 ዝርያ በዩኬ ከ16 ሰዎች መካከል አንዱ በቫይረሱ እንደሚያዝ በተደረጉ ምርመራዎች ተረጋግጧል።
ይህም በድምሩ 4.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ መያዙን የሚያሳይ ሲሆን ከሳምንት በፊት የነበረው ከዚህ በአንድ ሚሊዮን የሚያንስ ወይም 3.3 ሚሊዮን ነበር።
ባለለፈው ሳምንት የወጣው ይህ መረጃ ቫይረሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ስርጭት የሚያንጸባርቅና ትክክለኛው አሃዝን የሚያመላክት እንደሆነ ይታመናል።
በእንግሊዝ እና በዌልስ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ የጨመረ ሲሆን፣ በስኮትላንድ ከመጨመር አልፎ እስካሁን ያልተየ ቁጥር ተመዝግቧል። በተቃራኒው በሰሜን አየርላንድ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ማሽቆልቆል ጀምሯል።
በዩናይትድ ኪንግደም ያለው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ
- እንግሊዝ፡ ባለፈው ሳምንት ከነበረበት 4.9 በመቶ ወደ 6.4 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን 16 ከሚሆኑ ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ይያዛል።
- ዌልስ፡ ባለፈው ሳምንት ከነበረበት 4.1 በመቶ ወደ 6.4 በመቶ ከፍ ብሏል፣ በተመሳሳይ 16 ከሚሆኑ ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ይያዛል።
- ሰሜን አየርላንድ፡ ባለፈው ሳምንት ከነበረበት 7.1 በመቶ ወደ 5.9 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ከ17 ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ይያዛል።
- ስኮትላንድ: ባለፈው ሳምንት ከነበረበት 7.15 በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ከ11 ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ይያዛል እንደማለት ማለት ነው።
ምንም እንኳን ክትባቶች አሁንም በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሱ ቢታመንም፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከበረከቱ በዩናይትድ ኪንግደም ለኮሮናቫይረስ ህክምና ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች እንደሚጨምሩ ይገመታል።
ባለፈው ሐሙስ በወጣው የመጨረሻ መረጃ መሰረት በዩኬ 17,440 የኮቪድ ታማሚዎች በሆስፒታል ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ለሌላ ህክምና ሄደው ቫይረሱ የተገኝባቸው ናቸው።
ከእነዚህ ህሙማን ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ [ቬንትሌተር] ህክምናቸውን መከታተል ያለባቸው ናቸው።












