ታሊባን ሴቶች ያለ ወንድ ጠባቂ ረዥም ርቀት እንዳይጓዙ አዘዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍጋኒስታን ሴቶች ያለ ወንድ ጠባቂነት ረዥም ርቀት እንዳይጓዙ ታሊባን አዘዘ።
ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሴቶች የመጓጓዣ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት አብሯቸው የሚጓዝ ወንድ ጠባቂ ካለ ብቻ ነው ተብሏል።
ኢስላማዊው ታሊባን ባለፈው ነሐሴ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ የሴቶችን መብት የሚጋፉ ሕጎች በተከታታይ ሲያወጣ ቆይቷል።
ሴቶች ያለ ጠባቂ ረዥም ርቀት እንዳይጓጓዙ የታገደው ትላንት ነው።
ከዚህ በፊት ከወጡ የሴቶችን ነጻነት የሚገፉ ሕጎች መካከል ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዳያገኙ፣ እንዲሁም እንዳይሠሩ የሚከለከሉት ይጠቀሳሉ።
የመብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች፤ የረዥም ርቀት ጉዞ ላይ የተጣለውን ክልከላ "ሴቶችን እስረኛ የሚያደርግ" ሲል ኮንኖታል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ተባባሪ ዳይሬክተር ሄዘር ባር "ሴቶች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ያግዳል። በቤታቸው ጥቃት ሲገጥማቸው እንዳያመልጡም ይከለክላል" ብላለች።
የታሊባን የማስታወቂያ እና እሴት ሚኒስቴር እንዳለው፤ ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሄዱ ሴቶች የቅርብ ቤተሰብ ከሆነ ወንድ ጋር ብቻ ነው መጓዝ የሚፈቀድላቸው።
ካቡል ውስጥ የምትሠራው አዋላጅ ፋጢማ "ሕጉ በጣም አሳዝኖኛል። ነጻነቴን ነው የሚያሳጣኝ። ባለቤቴ ሳይኖር እኔ ወይም ልጄ ብንታመም ምን ሊውጠን ነው?" ብላለች።
ፋጢማ "ታሊባን ደስታችንን ቀምቶናል። ደስታዬንም ነጻነቴንም ተነጥቄያለሁ" ስትል ለቢቢሲ አስተያየቷን ሰጥታለች።
አዲስ የወጣው ሕግ ጨምሮ እንደሚለው ባለ መኪኖች ሂጃብ ወይም ሌላ ዓይነት መሸፈኛ ያላደረገችን ሴት ማሳፈር አይችሉም።
መኪና ውስጥ ሙዚቃ መክፈትም ተከልክሏል።
አሜሪካ እና አጋር ኃይሎቿ አፍጋኒስታንን ትተው ሲወጡ ሥልጣን የተቆጣጠረው ታሊባን ሴት ሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው ማገዱ ይታወሳል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ ወንድ ታዳጊዎችን ብቻ እያስተማሩ ይገኛሉ።
ታሊባን የጣላቸው ክልከላዎች "ጊዜያዊ ናቸው" ይላል። እገዳዎችን መጣል ያስፈለገው የሥራ እና የትምህርት ተቋማት ለሴቶች "ደኅንነታቸው የተጠበቀ" መሆኑ እስከሚረጋገጥ ድረስ ነው ብሏልም።
ታሊባን በ1990ዎቹ ሥልጣን ላይ ሳለ ሴቶች ከትምህርት እና ሥራ ታግደው ነበር።
ባለፈው ወር ሴቶች በቴሌቭዥን ድራማ እንዳይተውኑ ታዟል።
ሴት ጋዜጠኞችና የቴሌቭዥን መርሀ ግብር መሪዎች ሂጃብ እንዲያደርጉ ተወስኗል።
ለጋሽ አገራት ለአፍጋኒስታን የገንዘብ ድጎማ የሚሰጡት የሴቶች መብት ሲከበር ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ታሊባን ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ አፍጋኒስታን ታገኝ የነበረው ዓለም አቀፍ ድጎማ ተቋርጦባታል።
ይህም ሰብአዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሱን አባብሶታል።












