የሶሪያው ፕሬዝዳንት አሳድ ታሪካዊ የታባለ ጉብኝት በአረብ ኤምሬትስ አደረጉ

ታትሟል

የሶሪያው የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከ11 ዓመታት በኋላ ፕሬዝዳንት ባሻር አሳድ የመጀመሪያቸውን የአረብ አገር ጉብኝት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አድርገዋል።

ጉብኝቱ በጦርነቱ ምክንያት አሳድን አግልለው የነበሩ የአረብ አገራት ዳግም ግንኙነታቸውን ሊያድሱ እንደሚችሉ አመላካች ነው ተብሏል።

ሆኖም አሜሪካ ጉዞው "በጣም ቅር አሰኝቶኛል" ብላለች።

ፕሬዝዳንት አሳድ በጉብኝታቸው ኤምሬትስ ውስጥ ካገኟቸው ሰዎች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ውዝግቦች ስማቸው የሚናሳው የዱባዩ ቢልየነር ሼክ መሐመድ አል ማክቱም አንዱ ናቸው።

ባለሐብቱ ካሏቸው 25 ልጆች መካከል አንዷ የሆነችው ላቲፋ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ከዱባይ ለማምለጥ ያደረገችው ሙከራ ከከሸፈ በኋላ አሁን ታግታ እንደምትገኝ ተናግራ ነበር። እናም አሳድ ያገኟቸው እኚህ ባለሐብት በዚህ እና በሌሎች ጉዳዮች ስማቸው ይብጠለጣላል።

በተጨማሪም አሳድ ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ዋና ከተማ አቡዳቢ በመጓዝ ከልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ለመገናኘት ችለዋል።

"ሶሪያ ለአረብ አገራት ደኅንነት ቁልፍ እንደሆነች እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአገሪቱ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን" የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መሪዎቹ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሶሪያ ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ በምትችልበት መንገድ እንዲሁም በአገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን የኢኮኖሚና ንግድ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንት አሳድ ከማንቸስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ሼክ መንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ፎቶ ሲነሱም ታይተዋል።

የሶሪያ ፕሬዝደንት በአገራቸው ከአስር ዓመት በፊት በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ 350,000 ሰዎችን መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያመለከተ ሲሆን፣ ባሻር አል አሳድ ከጦርነት መጀመር ወዲህ በጣም ጥቂት ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን ብቻ ነው ያደረጉት።

ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ፕሬዝዳንት አሳድ በጦርነት የምትታመሰውን አገራቸውን ለቀው ወታደራዊ ድጋፍ ወደ ሚያደርጉላቸው ሩሲያ እና ኢራንን ተጉዘዋል።

የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አሳድን ለመቀበል መወሰኗ በጣም አሳዛኝ እና ቅር የሚያሰኝ ነው ስትል አሜሪካ ገልጻለች።

አሜሪካ በሶሪያ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነትን መፍትሄ ለመስጠት መሻሻል እስኪታይ ድረስ ከሶሪያ መሪ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትቃወም ትገልጻለች።

እንደ አብዛኞቹ የአረብ አገራት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የበሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከአገሪቱ ጋር ግንኙነቷን አቋርጣ የነበረ ሲሆን፣ የአማፅያኑ ተዋጊዎች የአሳድን መንግሥት ለመጣል ያደረጉትን ሙከራ የደገፈችበት ወቅትም ነበር።

ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ሲሆን ከአሜሪካ ተቃውሞ ቢያጋጥማትም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ሶሪያን ከአረቡ ዓለም ጋር የነበራትን የቀድሞ ግንኙነት ለማደስ ጥረት እያደረገች ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዳግም የከፈተች ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ዲፕሎማቶች ፕሬዚዳንት አሳድን እንዲያገኙ ልካ ነበር።