'ዴልታክሮን' ስለተባለው ስለአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምን እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳይንቲስቶች አዲስ የኮቪድ-19 ዝርያ መለየታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ከሳምንት በፊት አስታውቋል።
የዴልታ እና የኦሚክሮን ዝርያዎች ጥምረት በመሆኑም ይፋዊ ባልሆነ መንገድ "ዴልታክሮን" ተብሎ ስም ተሰጥቶታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን ዝርያ በይፋ ኤዋይ.4/ቢኤ.1 ሲል ይገልጸዋል። እስካሁን ድረስም ቫይረሱ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር "አስጨናቂ" ዝርያ ነው ብሎ አይቆጥረውም።
"የዴልታክሮን" ዝርያ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ተገኝቷል።
ሳይንቲስቶች እና የጤና ባለሙያዎች ስለ አዲሱ ልውጥ ዝርያ እርግጠኛ አይደሉም። በተለይም በፍጥነት ስለመተላለፉ፣ ክትባቶችን ስለመቋቋሙ ወይም ከባድ ምልክቶችን የሚያስከትል ስለመሆኑ አያውቁም።
እስካሁን ስለ ዝርያው ምን እናውቃለን?
አመጣጥ እና ስርጭት
የመጀመሪያዎቹ የ"ዴልታክሮን" ዝርያዎች ጥር ወር ላይ ፈረንሳይ ስለመገኘታቸው ተረጋግጧል።
ቀጥሎም በቤልጂየም፣ በጀርመን፣ በዴንማርክ እና በኔዘርላንድስ ተገኝቷል ሲል 'ጊሳይድ' የተባለ እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሳይንቲስቶች ስለ ኮሮናቫይረስ የዘረመል መረጃን የሚያጋሩበት በይነ መረብ አስታውቋል።
በቅርቡ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በብራዚል የ"ዴልታክሮን" ዝርያዎች ተስተውለዋል።
ከዝርያው ጋር የተገናኙ ቁጥሮች አሁንም በጣም ዝቅተኛ ናቸው። ከመጋቢት 15 ጀምሮ ለጊሳይድ 47 የኤዋይ.4/ቢኤ.1 ናሙናዎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 36ቱ ከፈረንሳይ የተገኙ ናቸው።
ተጨባጭ መረጃ ባይሆንም የ"ዴልታክሮን" ቁጥር ከጥር እስከ መጋቢት ወር ድረስ በከፍተኛ ደረጃ አለማደጉ ዝርያው ከዴልታ እና ከኦሚክሮን የበለጠ እንደማይተላለፍ እንደ ቅድመ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ይህንን የሚያረጋግጡ 'ሄሊክስ' ከተሰኘው እና በዩናይትድ ስቴትስ በዘረ መል ላይ ከሚሠራው የግል ኩባንያ ተመራማሪዎች ገና ካልታተመ ጥናት የተገኙ ተጨማሪ መረጃዎች ናቸው።
ሳይንቲስቶች በኅዳር 2013 ዓ.ም እና ጥር 2014 መካከል የተሰበሰቡ ከ29,000 በላይ የኮቪድ-19 ናሙናዎችን ተንትነዋል። ይህ ወቅት የዴልታ እና የኦሚክሮን ዝርያዎች በአሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጩበት ነው።
ከእነዚህ ናሙናዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ከ"ዴልታክሮን" ጋር ተያያዥ ነበሩ።
ጥናት አድራጊዎቹ እነዚህ "አልፎ አልፎ" የሚከሰቱ እና "የዴልታ-ኦሚክሮን ጥምረት ከኦሚክሮን ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸሩ የበለጠ ስለመተላለፋቸው የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም" በማለት ደምድመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተለዋጭ ዝርያዎች እንዴት ይደባለቃሉ?
በብራዚሉ ፊዮክሩዝ የሕብረተሰብ ጤና ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቫይረሶች ምርምር ባለሙያው ፌሊፔ ናቬካ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተለያዩ ዝርያዎች አዲስ ዝርያን ለመፍጠር መቀላቀላቸው ያልተለመደ ወይም ያልተጠበቀ ነገር አይደለም።
"ይህ ቀደም ሲልም ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ብዙ ጊዜ ተከስቷል። ሲጀምር የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን አንዳቸው ከሌላው በጣም የተለዩ ስላልሆኑ እነዚህን ክስተቶች መለየት አስቸጋሪ ነው።"
አክለውም "ቫይረሶች በየጊዜው እየተለወጡ ናቸው። አዳዲስ ዝርያዎች መፈጠራቸው ሁሌም መጥፎ ነገር አይደለም። ይህ በወረርሽኙ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ መገምገም እና መረዳት አለብን" ብለዋል።
ይህ ጥምረት በተግባር እንዴት ይከሰታል?
በመጀመሪያ ባለፉት ጥቂት ወራት ዴልታ እና ኦሚክሮን የተሰኙ ሁለት የኮሮናቫይረስ ዓይነቶች በከፍተኛ ስርጭት ላይ መቆየታቸውን ልብ ልንል ይገባል።
በዚህ መሠረት አንድ ግለሰብ በቡና ቤት፣ በሕዝብ ማመላለሻዎች ወይም በማንኛውም ሕዝብ በተጨናነቀበት ቦታ ሁለቱም ቫይረሶች ካሉባቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ ሊያዝ ይችላል።
ሁለቱ ዝርያዎች በአንድ ጊዜ ሊበክሉ ይችላሉ። በውጤቱም የቫይረሱ አዲስ ድቅል የዴልታ እና የኦሚክሮን የዘረመል ባህሪያትን ይይዛል።
ሆኖም የሁለቱ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች "መደባለቅ" የበለጠ ሆስፒታል የመግባት ምጣኔን ወይም የመሞት አደጋን ሊያስከትል ይችላል ወይ የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከዚህ ቀደም በኮሮናቫይረስ በመያዝ ምክንያት ወይም በክትባት በተፈጠረ የመከላከል አቅም ሳቢያ ከቫይረሱ ማምለጥ ስለመቻሉ ምንም መረጃ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መጨነቅ ይኖርብን ይሆን?
አዲሱን ዝርያ በተመለከተ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ባለሥልጣናት መረጋጋትን ጠይቀዋል። የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) "ዴልታክሮንን" ሥጋት የሚፈጥር ሲሉ አልሰየሙትም።
የዓለም ጤና ድርጅት "በክትትል ላይ ያለ ዝርያ" ሲል መድቦታል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ቴክኒክ ቡድን መሪ የሆኑት ማሪያ ቫን ኬርክሆቭ መጋቢት 9 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ከዚህ ዝርያ ጋር በተያያዘ በወረርሽኝ ወይም በበሽታው ክብደት ላይ ምንም ለውጦች አልታዩም" ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
"እንደ አለመታደል ሆኖ እነዚህ ቫይረሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለወጡ ስለሆነ አሁንም የተዋሃዱ ቫይረሶችን እንደምናይ እንጠብቃለን" ብለዋል።
ፌሊፔ ናቬካ በበኩላቸው የአዲስ ዝርያ መፈጠር የሳይንቲስቶችን የዝርያ ክትትል አስፈላጊነትን ያጠናክራል ብለዋል።
"ይህ አዲስ ዝርያ ምን አይነት ተጽእኖ እንዳለው ለመረዳት ናሙናዎችን ደጋግመን መሥራት አለብን" ሲል ጠቁሟል።.
ናቬካ ሰዎች ሁሌም በተጠንቀቅ ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።
"ከግለሰብ አንጻር የክትባት መርሃ ግብሩን በተፈቀደው ልክ ማጠናቀቅ በጣም አስፈላጊ ነው" ሲሉም ይመክራሉ።
የቫይረሶች ጥናት ባለሙያው "በኮሮናቫይረስ የመያዝ ዕድልን ለመቀነስ እንደ እጅ መታጠብ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ ጭንብል መልበስን የመሳሰሉ የመከላከያ እርምጃዎች መሥራታቸውን ቀጥለዋል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images














