ሕንድ ወደ ፓኪስታን ሚሳኤል ያስወነጨፍኩት ተሳስቼ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሕንድ ረቡዕ ዕለት ወደ ፓኪስታን ሚሳኤል ማስወንጨፏን ተከትሎ ይቅርታ ጠየቀች።
ነገሩ የዘውትር ጥገና በሚደረግበት ወቅት በተፈጠረ ቴክኒካዊ ስህተት የሆነ ነው ከማለት ውጪ ሕንድ ስለክስተቱ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠችም።
ሕንድ ክስተቱ እንደጸጸታት፣ ያም ሆኖ የሰው ሕይወት አለመጥፋቱ ደግሞ እፎይታን እንደሰጣት ገልጣለች።
የፓኪስታን መከላከያ በበኩሉ "ፈጣን የሆነ አንዳች በራሪ ቁስ በምሥራቅ ሚያን ቻኑ ግዛት አካባቢ መውደቁን" ገልጦ ነበር።
ቁሱ የተምዘገዘበት ሁኔታም የጉዞ አውሮፕላን ላይ አንዳች እክል ለመፍጠር በሚችልበት ሁኔታ እንደነበር ገልጧል።
የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር ጉዳዩን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ እንደሚለው "ክስተቱ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ" በፍርድ ቤት እንዲጣራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ፓኪስታን በበኩሏ እንዲህ አይነቱ የሕንድ እንዝህላልነት ብዙ ጣጣ ሊያስከትል እንደሚችል ልብ ልትል ይገባል ብላለች።
ይህ ሚሳኤል የተተኮሰው ከሲርሳ፣ ሐሪያና ግዛት ነው።
የፓኪስታን የአየር ኃይል እንዳረጋገጠው ይህ ሚሳኤል ከድምጽ ሦስት እጥፍ በሚሆን ፍጥነት በ40ሺህ ጫማ ከፍታ 124 ኪሎ ሜትር በፓኪስታን የአየር ክልል ተምዘግዝጎ ነው የወደቀው።
የተምዘገዘገበት አቅጣጫና ከፍታም በርካታ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የአየር በረራዎችን አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል መልኩ ነበር።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት አርብ በጉዳዩ ዙርያ ማብራሪያ ለመጠየቅ የሕንድ አምባሳደር ተወካይን ጠርቶ ማነጋገሩ ተሰምቷል።
ፓኪስታን በትክክል ምን ስህተት ተፈጥሮ ሚሳኤሉ ወደ ግዛቷ እንደተወነጨፈ ምርመራ ተደርጎ የምርመራ ውጤቱ ቅጂ በቶሎ እንዲሰጣት ጥያቄ አቅርባለች።
ፓኪስታን እና ሕንድ የኑክሊየር ታጣቂ አገራት ናቸው።












