ኬንያ በኮቪድ ምክንያት ጥላቸው የነበሩ ግዴታዎችን አላላች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል ለሁለት ዓመት ያህል ደንግጋቸው የነበሩ ግዴታዎችን እንዲነሱ መወሰኗን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዚህም ከአሁን በኋላ ሰዎች ከቤት ውጪ የአፍና የአፍነጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ እንደማይሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ዜጎች በቤት ውስጥ በሚደረጉ መሰባሰቦችና በሕዝብ ትራንስፖርቶች ውስጥ ጭምብል እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ መክሯል።
ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል አሁንም ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች አካላዊ ርቀትና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ ተግባራዊ መሆኑ ይቀጥላል።
በወረርሽኙ የታዙ ሰዎች ተለይተው እንዲቆዩ ይደረግ የነበረው ግዴታም እንዲቀር ተደርጓል።
ተሳታፊዎች በሙሉ ከተከተቡ በቤት ውስጥ የሚደረጉ ስብሰባዎች እና የአምልኮት መሰባሰቦች በሙሉ አቅማቸው እንዲካሄዱ ተፈቅዷል።
የኬንያው የጤና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ እንዳሉት የአገሪቱ የእምነት ተቋማት ምክር ቤት የአምልኮ አገልግሎቶች በሚጀመሩበትና በሚከናወኑበት ሁኔታ ላይ ዝርዝር መመሪያዎችን ያወጣሉ።
የኬንያ መንግሥት ይህን እርምጃ የወሰደው በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኮቪድ-19 መስፋፋት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ነው። የጤና ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፈው ወር የበሽታው መስፋፋት ምጣኔ ከ5 በመቶ በታች ሆኖ ቀጥሏል።
ኬንያ ሁሉም ዜጎቿ የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ ጥረት እያደረገች ሲሆን፣ አስካሁን ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ ሙሉውን ክትባት ወስዷል። ይህም መከተብ ከሚገባው ከአጠቃላዩ ሕዝብ 28.5 በመቶ ነው።
ኬንያ የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን ግዴታ ያደረገችው የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ ስጋት በነበረበት ከሁለት ዓመት በፊት ነበረ።












