ሱዳናዊ እና አፍጋናዊ ዜጎች በአነስተኛ ጀልባ ስደተኞችን ወደ ዩኬ በማመላለስ ተከስሰው ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, CPS
ሁለት ግለሰቦች በአነስተኛ ጀልባ ስደተኞችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲያቋርጡ በማድረግ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል በሚል አዲስ በጸደቀ ሕግ መሠረት ታሰሩ።
ሱዳናዊው አልኑር ሞሐመድ አሊ በሚያዚያ ወር 74 ሰዎችን በአንዲት አነስተኛ ጀልባ ጭኖ ማጓጓዙን በማመኑ የ27 ወራት እስር ተፈርዶበት ነበር።
ሁለተኛው ተከሳሽ አፍጋኒስታናዊው ሞሐመድ ታጂክ በጥር ወር አደገኛ በሆነ የአየር ሁኔታ ጀልባዎችን እንዲቀዝፉ በማድረግ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ሁለቱም ስደተኞች በዚህ ዓመት ሥራ ላይ በዋለው የድንበር፣ ደኅንነት፣ ጥገኝነት እና ስደተኞች ሕግ መሠረት በባሕር ላይ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣላቸውን አምነዋል።
ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በአነስተኛ ጀልባ ስደተኞችን በማመላለስ ለሞት ወይንም ለከፍተኛ አደጋ እንዲጋለጡ የሚያደርጉ ሲሆን ሕጉ ጀልባዎችን የሚቆጣጠሩ እና የሚቀዝፉ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው።
እነዚህ አነስተኛ ጀልባዎች እአአ በ2018 ብቻ ከ200,000 በላይ ስደተኞችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አሻግረዋል።
ተከሳሾቹ በቀረበባቸው አዲስ ክስ የሁለቱም ጥፋት ተመሳሳይ ሆኖ በመገኘቱ ረቡዕ ዕለት በካንተርቤሪ ክራውን ችሎት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ችሎቱ ሁለቱም ተከሳሾች ይዘውሯቸው ነበር ያሏቸውን ጀልባዎች በተመለከተ ለችሎቱ የድሮን ምሥሎችን ተመልክቷል።
የ26 ዓመቱ አሊ የሚያሽከረክረው ጀልባ በሰዎች የተጨናነቀ የነበረ ሲሆን ስደተኞች ወደ ጀልባዋ ጫፍ ተጠግተው እግራቸው የባሕሩን ውሃ ይነካ እንደነበር ታይቷል።
እአአ በሚያዚያ 9 በጀልባዋ ላይ የነበሩት አብዛኞቹ ስደተኞች የሕይወት አድን ጃኬት አለመልበሳቸውም ተስተውሏል።

የፎቶው ባለመብት, CPS
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም ሁለት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በሰሜናዊ ፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ ወደ ጀልባው ለመሳፈር ሲሞክሩ ሰምጠው መሞታቸውን ተናግረው ነበር።
የብሪታኒያ አቃቢያነ ሕጎች ግን ለሞታቸው ሁለቱ ተከሳሾች ተጠያቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
በወቅቱ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ከ40 በላይ ስደተኞች ማዳናቸውን አስታውቀዋል።
የአሊ ጠበቃ ስለ ሞቶቹ የተሳሳተ ዘገባ መኖሩን በመግለጽ ደንበኛዬ ላይ "ከባድ ተጽዕኖ" አስከትሎበታል ብሏል።
አሊ በተወነጀለበት ጥፋት "የተሳሳተ መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን በመስጠት" የብሔራዊ ወንጀሎች ኤጀንሲን ተጠያቂ አድርገዋል።
የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ሳይመን ጀምስ የብሪታንያ ባለሥልጣናት አሊ በፈረንሳይ ባሕር ዳርቻ ለሞቱት ስደተኞች ተጠያቂ ነው የሚለው "የተሳሳተ መረጃ" መሆኑን ተናግረዋል።
ችሎቱ የ32 ዓመቱ ታጂክ ጥር 17 በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ውስጥ የሚቀዝፋትን ጀልባ የሚያሳይ ሌላ ምሥል ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።

የፎቶው ባለመብት, CPS
ታጂክ በሚቀዝፈው ጀልባ ላይ የተሳፈሩ በርካታ ስደተኞች ምንም እንኳን የአየር ሁኔታው ከባድ ቢሆንም የሕይወት አድን ጃኬት አልለበሱም።
ችሎቱ አሊ ከሱዳን የተሰደደው እአአ በ2019 የሚኖርበት መንደር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ተናግሯል።
መጀመርያ ወደ ሊቢያ የተጓዘ ሲሆን ሁለት ጊዜ ታስሮ ስቅይት ተፈጽሞበታል።
ችሎቱ የአሊ ቤተሰቦች በዳርፉር ይኖሩ እንደነበር እና አሁን በሕይወት ስለመኖራቸው ምንም መረጃ እንደሌለ አድምጧል።
ታጂክን የወከለው የሕግ ባለሙያ በበኩሉ አባቱ እና ወንድሙ በታሊባን ታጣቂዎች ከአስር ዓመት በፊት አፍጋኒስታን ውስጥ መገደላቸውን ተናግረዋል።
ታጂክ በታሊባን ጥቃት እንደሚደርስበት በመፍራቱ ወደ ግሪክ ተሰድዶ ጥገኝነት መጠየቁን ከዚያም ወደ ፈረንሳይ መጓዙን ተናግሯል።
ሁለቱም ተከሳሾች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረገውን ፍልሰት በማመቻቸትም ሆነ ጀልባዎቹን በማንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚያገኙ አልተገለጸም።
አሊ ጀልባዎቹን እንዲያሽከረክር በፈረንሳይ የሚገኙ ታጣቂዎች እንደሚያስገድዱት ተናግሯል።
አቃቤ ሕግ ግን ሁለቱም ግለሰቦች ጀልባዎቹን ለማሽከርከር ፈቃደኛ በመሆናቸው የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣላቸውን በመጥቀስ ተከራክሯል።
ዳኛው ሁለቱም ግለሰቦች በዩናይትድ ኪንግደም የጥገኝነት መብት ቢኖራቸውም ውሳኔው ግን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ መሆኑን ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ የእስር ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላ ከአገሪቱ ለቅቀው ይወጣሉ ወይስ እዚያው ይቆያሉ የሚለው እስካሁን አልታወቀም።
አዲሱ ሕግ አነስተኛ ጀልባዎችን የሚያንቀሳቅሱ ሰዎችን ዒላማ ለማድረግ የወጣ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ9,000 በላይ ሰዎች አነስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ ዮኬ ገብተዋል።
በአነሰተኛ ጀልባዎች ተሳፍረው ወደ ዩኬ 46,000 ስደተኞች የገቡት እአአ በ2022 ነው።















