ናይጄሪያ የጥቃት ዒላማ የሆኑ ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ ማስወጣት ጀመረች

ከናይሪያውያኑ አንዱ ሚኪና ውስጥ ተቀምጦ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ደብብ አፍሪካ ውስጥ የተፈጠረውን ፀረ አፍሪካውያን ስደተኞች ተቃውሞ በመሸሽ የመጀመሪያዎቹን 270 ወደ አገራቸው የሚመለሱ ናይጄሪያውያንን የያዘ አውሮፕላን ከጆሃንስበርግ ተነሳ።

ሕጋዊ ባልሆኑ ስደተኞች ላይ በመላው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለሳምንታት እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በመፍራት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ናይጄሪያውያን አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ተመዝግበዋል።

ዛሬ ሐሙስ ጆሃንስበርግ ከሚገኘው ኦአር ታምቦ አየር ማረፊያ በተነሳው አውሮፕላን ከተሳፈሩት ናይጄሪያውያን መካከል ከ20 ዓመታት በላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኖሩ ይገኙባቸዋል።

ተቃዋሚዎች ስደተኞቹ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ አገሪቱን ለውቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ሲሆን፣ ይህም ጥቃት የሚጋብዝ ማስጠንቀቂያ በስደተኞች መካከል ፍርሃት በመፍጠር ከደቡብ አፍሪካ እንዲለቁ እንዳደረጋቸው እየተነገረ ነው።

በተቃዋሚዎች ጥቃት የተገደሉ አፍሪካውያን ስደተኞች መኖራቸው ቢነገርም ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በተፈጸሙ በመጤ ጠል ጥቃቶች እስካሁን ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የሚያመለክት ይፋዊ አሃዝ የለም።

ፖሊስ ሁለት የሞዛምቢክ ዜጎች ዌስተርን ኬፕ በሚባለው ግዛት ውስጥ ከሳምንት በፊት መገደላቸውን ቢያሳውቅም የግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ አልገለጸም። ነገር ግን የሞዛምቢክ ባለሥልጣናት በርካታ ዜጎቻቸው መገደላቸውን እና ምክንያቱም የመጤ ጠል ጥቃት ነው ብለው ያምናሉ።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደቡብ አፍሪካውያን በአገሪቱ ከ30 አስከ 40 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ለሚገመተው የሥራ አጦች ቁጥር እንዲሁም በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ተቋማት ላይ ለተፈጠረው ጫና አፍሪካውያን ስደተኞችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ የናይጄሪያ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ኦኬይ-ኡቼ ለቢቢሲ "በደቡብ አፍሪካ ያሉት ስደተኞች ከስምንት በመቶ ያልበለጠ ነው" በማለት በአገሪቱ ውስጥ ላለው ችግር ሁሉ ስደተኞችን እንደምክንያት ማቅረብ ትክክል አይደለም ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባደረጉት በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ላይ በስደተኞች ላይ ለተነሳው ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ሕጋዊ ባልሆኑ ስደተኞች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን አሳውቀዋል።

ይህም ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን የቀጠሩ አሠሪዎች እንዲታሰሩ የሚያደርግ፣ የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከት እና ከአገር ማስወጣትን የሚያፋጥን የተለየ ችሎት እንዲቋቋም እና የእያንዳንዱን ስደተኛ መረጃ በዝርዝር እንደሚያዝ አሳውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ዜጎቻቸው በስደተተኞች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቀዋል።

ነገር ግን የናይጄሪያዋ ዲፕሎማት ፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት እየሆነ ያለውን ነገር በመቃወም ትክክለኛውን ነገር ቢናገሩም፣ "ጎዳናዎች ላይ የስደተኞችን ሕይወት ስቃይ ያደረጉ የሚታወቁ ሰዎች በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ አልተጠየቁም" በማለት መንግሥት የጥላቻ ቅስቀሳ በሚያደርጉት እና ስደተኞችን በሚያጠቁት ላይ ግልጽ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።