አይኤስ የመሪውን አልቁራይሺ መሞት አምኖ፤ ተተኪ መሪ ሾመ

አቡ ኢብራሒም አልቁራይሺን

የፎቶው ባለመብት, US DEPARTMENT OF STATE

የምስሉ መግለጫ, አቡ ኢብራሒም አልቁራይሺን
ታትሟል

ኢስላሚክ ስቴት ወይም በእንግሊዝኛ የምህጻር ቃል አይኤስ (IS) የተሰኘው ጽንፈኛ ቡድን የመሪውን የአቡ ኢብራሒም አልቁራይሺን መገደል አመነ፡፡

በድረ ገጽ በተለቀቀ አንድ የድምጽ መልእክት አቡ አልሐሰን ሐሸሚ አልቁራይሺ አዲሱ መሪ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህ እጩ መሪ ትክክለኛ ስሙና ማንነቱን ግን ይፋ አልተደረገም፡፡

በዚህ የድምጽ መልእክት እስከዛሬ ቡድኑን ሲመራ የነበረው አቡ ኢብራሒም አልቁራይሺ የት፣ በማንና እንዴት እንደተገደለ ያለው ነገርም የለም፡፡

አሜሪካ እንደምትለው ግን አልቁራይሺን ለመያዝ ልዩ ዘመቻ በተደረገበት ወቅት ከበባ ላይ መሆኑን ሲረዳ ራሱንና ቤተሰቡን በቦምብ አጥፍቷል፡፡

ይህም የሆነው፣ እንደ አሜሪካ መረጃ፣ በየካቲት 3 በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ከተደበቀበት ሥፍራ ነው፡፡

ጆ ባይደን የአል ቁራይሺ ሞት ለዓለም የሽብር ሰንሰለት መዳከም አንዳች አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረው ነበር፡፡

አልቁራይሺ የሽብር ድርጅቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስፋፋት ይታወቃል፡፡

ከዚህም ባሻገር ያዚዲ የተሰኙ የኢራቅ ህዳጣን ማኅበረሰቦችን ጭፍጨፋ እንደመራ አሜሪካ ትጠረጥራለች፡፡

የትናንት ሐሙስ የድምጽ መልእክት የተላለፈው በአይኤስ ቃል አቀባይ አቡ ኡመር አል ሙሐጂር ድምጽ ነው፡፡

አል ሙሐጂር እንዳለው ከርሱ በፊት የቡድኑ ቃል አቀባይ የነበረው ሐምዛ ቁራይሺም በቅርቡ ተገድሏል፡፡

ሙሐጂር በዚህ የድምጽ መልእክት እንዳለው የአዲሱን መሪ ትክክለኛ ስም ለመግለጽ እንደሚቸገር ነገር ግን ሁሉም የአይኤስ አባላት ለርሱ ታማኝ ሆነው እንዲገዙ አሳስቧል፡፡

በርካታ ተንታኞች ግን አዲሱ የአይ ኤስ መሪ ኢራቃዊው በሸር ከታብ ጋዛል አል ሱማይዳይ ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠረጥራሉ፡፡

ይህ ሰው በአጭር ስሙ አቡ ከታብ አል ኢራቂ በሚል ይታወቃል፡፡

አይኤስ በአንድ ወቅት 88ሺህ ሰኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሰፋውን በምሥራቅ ኢራቅ እስከ ምዕራብ ሶሪያ የሚዘረጋ ግዛትን ሰጥ-ለጥ አድርጎ ሲመራ የነበረ ድርጅት ነው፡፡

አይአስ በዚህ ወቅት 8 ሚሊዮን ሕዝቦችም በሥሩ አስተዳድሯል፡፡

ይህ ቡድን በፈረንጆቹ 2019 የመጨረሻ የቁጥጥር ቀጠናው ከነበረችው የኢራቅ ክፍል በጦርነት ተሸንፎ ሲወጣ እስከ 10ሺ ተዋጊዎች ነበሩት፡፡

የአቡ ኢብራሒም አል ቁራይሺ ሞት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ባለችው ኢድሊብ የተሰማው አይኤስ መጠነ ሰፊ ጥቃት በኩርዲሽ እስር ቤት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር፡፡

በዚህ ጥቃት 121 የእስር ቤት ጠባቂዎች እና የኩርድ ሚሊሻዎች ተገድለዋል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመርያም አይኤስ በማዕከላዊ ሶሪያ በረሃ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት 15 የሶሪያ ወታደሮች ላይ ግድያ ፈጽሟል፡፡