ጂቡቲ ከሙስና ጋር በተያያዘ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣኖቿን አሰረች

ታትሟል

በጂቡቲ እያካሄደ ካለው የፀረ ሙስና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።

ባለሥልጣናቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሕዝብ ሀብት ምዝበራ ጋር በተያያዘ በቀለበባቸው ክስ ምርመራ ሊደረግባቸው መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ባሉ ዋነኛ ክፍሎች ውስጥ ኃላፊዎች ናቸው።

ፋራህ ሞሐመድ ኦስማን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ምክትል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ሳላህ ሰይድ አዋሌህ ደግሞ በሚኒስቴሩ የግምጃ ቤት ኃላፊ ናቸው ተብሏል።

የባለሥልጣናቱ የታሰሩት የአገሪቱ ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምርመራ ካደረገ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥት ገንዘብ ምዝበራ መፈጸሙን ካረጋገጠ በኋላ መሆኑን የጂቡቲ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በምርመራ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው አንዳንድ ነጋዴዎች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ካሉት ከእነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተጭበረበረ ስምምነት ተደርጓል ሲል የቴሌቪዝን ጣቢያው ዘገባ አመልክቷል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የጂቡቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለእስር ዳርጓቸዋል ተብሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም።

የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጨምሮ እንዳለው ይህ የባለሥልጣናቱ አስር የተገለጸው "በርካታ የጂቡቲ ነጋዴዎችና ሌሎች ሰዎች በፖሊስ መያዛቸውን ተከትሎ ነው።"

በጂቡቲ አልፎ አልፎ ከሚዘገብ የሙስና ክስተት ውጪ የአገሪቱ መንግሥት የጎላ እርምጃን ሲወስድ እምብዛም አይታይም።

ከሕንድ ውቅያኖስ ወደ ቀይ ባሕር በሚያስገባው መተላለፊያ ላይ የምትገኘው ስትራተጂካዊቷ የአፍሪካ ቀንድ አገር ጂቡቲ ከፍተኛውን ገቢዋን የምታገኘው በዋናነት ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው የወደብ አገልግሎት ነው።

በተጨማሪም በርካታ ታላላቅ አገራት በአገሪቱ ውስጥ የጦር ሰፈሮች ያሏቸው ሲሆን ይህም ለጂቡቲ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብና ድጋፍን እንደሚያስገኝላት ይታመናል።