ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያዊያን የዲቪ ዕድለኞች የጉዞ ሂደት ለምን አጣብቂኝ ውስጥ ገባ?
ዶ/ር ቲዮብስታ ተስፋዬ ወጣት ሐኪም ናት፡፡
በርካታ ምሩቅ ሐኪም ሥራ አጥ በሆነባት ኢትዮጵያ በሕክምና ዘርፍ የተመረቀችው የዛሬ 2 ዓመት ነበር፡፡
ለአንድ ዓመት ተኩል እንደነገሩ ሥራ ሞካክራለች፡፡
ከማዕረጓ የሚጣጣም ኑሮን ለማደላደል ደፋ ቀና ብላለች፡፡ መስመር አልይዝ እያለ አስቸገራት እንጂ፡፡
ባለፈው ግንቦት ግን ሕይወቷ በራ፡፡
እንደዋዛ የሞላችው ዲቪ በሯን አንኳኳ፡፡ ማመን አቃታት፡፡
ሕይወቷ ሊሰምር መሆኑ ተሰማት፡፡
ዶ/ር ቲዮብስታ ትልቁ ሕልሟ በአሜሪካን አገር የዕጩ ሐኪም መግቢያ ፈተና መውሰድ ነበር፡፡
በሕክምና ዘርፍ የላቀ ትምህርት ለመከታተል ስትቋምጥ ነው የኖረችው፡፡
ይህን ሕልሟን ሊያሳካ የሚችለው ዲቪ ያለችበት ድረስ መጥቶ 'እንኳን ደስ ያለሽ' ሲላት እንዴት አትደንግጥ፡፡
"በእኛ አገር አንድ ፊዚሺያን በወር የሚከፈለው ደመወዝ መቶ ዶላር አይሞላም" ትላለች፡፡
ከዚህ አንጻር የዲቪው ዕድል የተሻለ ዕድልን ይዞላት እንደሚመጣ ተስፋ አድርጋለች፡፡
ዶ/ር ቲዮብስታ ከዲቪው መምጣት በኋላ ባሉ ቀናት አእምሯዋ ውስጥ የሚመላለሰው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
አሜሪካ ሄዶ የእነሱን የሕክምና መግቢያ ፈተና (USMLE) መውሰድ፤ መማር፣ ማደግ፣ ማወቅ፡፡
"ያንን ብቻ ነበር የማውጠነጥነው፡፡ ያንን ሕልሜን ነው እያሰናከሉት ያሉት" ትላለች፡፡
ዲቪዋ ለምን ተሰናከለ?
ዶ/ር ቲዮብስታ ዲቪ ስትሞላ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ ሞክራለች፡፡
12ኛ ክፍል ካጠናቀቀች ወዲህ አንድም ጊዜ ዲቪ አምልጧት አያውቅም፡፡
"እኔ ራሴን ችዬ መሙላት ከመጀመሬ በፊት ደግሞ ወላጆቼ ይሞሉኝ ነበር፡፡ እነሱን እያየሁ ነው ያደግኩት" ትላለች፡፡
ይህ የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የወል ታሪክ ነው፡፡
ዲቪ ጥቂት ለማይባሉ ኢትዮጵያዊያን እንደው እግረ መንገድ የሚፋቅ ፈጣን ሎቶሪ አይደለም፡፡
በጸሎት የሚሞላ የነገ ተስፋ ነው፡፡ አንዳንዶችም ወደ ተሻለ ሕይወት የመሸጋጋሪያ ትኬት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ለዚህም ነው ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ ድል ያለ ድግስ ደግሶ የሚሸኘው፡፡
ዶ/ር ቲዮብስታም ብሥራቱን የሰማችበትን ቅጽበት የማትዘነጋው ለዚሁ ነው፡፡
"ግንቦት 8 ነበር ውጤት የተለቀቀው፤ እኔ በነገታው ነው ያየሁት፡፡ እንደደረሰኝ ሳውቅ በመደሰት ፈንታ ደነገጥኩ፡፡ ቤት ስነግራቸው ራሱ አላመኑኝም" ትላለች፡፡
ውጭ ለሚኖሩ አክስትና አጎቶቿ ሳይቀር ደውላ ዜናውን አብሥራለች፡፡
ይህ ሁሉ የቤተሰብ ደስታ ግን ቀዝቃዛ ውሃ ሊቸለስበት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ለቃለ መጠይቅ አልጋብዛቸው አለ፡፡ በወቅቱ ሁኔታ በሩን ገርበብ አድርጎ ዘግቶ ነበር፡፡ እነ ዶ/ር ቴዮብስታን ግን ጥርቅም አድርጎ ዘጋቸው፡፡ ለወራት ዝም እንዳለ ቀረ፡፡ ለምን?
የአሜሪካ ኤምባሲ ምን ይላል?
ዘንድሮ ዕድለኞቹን ከፍተኛ ሐዘን ላይ የጣለ ክስተት እንዴት ሊያጋጥም ቻለ? የሚለውን ይዘን አሜሪካ ኤምባሲ ምላሽ እንዲሰጥ በስልክ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም፡፡
ነገር ግን በቁጥር 2988 የሚሆኑ የዲቪ ዕድለኞች በመቦረቅ ፈንታ ትካዜ ውስጥ የከተታቸው አንዱ የኤምባሲው የተራዘመ ዝምታ እንደሆነ ተረድተናል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ዝምታ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አስታኮ እንደሆነ ከዕጩ ዕድለኞቹ ተገልጾልናል፡፡
አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የእነዚህን ዕድለኞች ጉዳይ ማስፈጸም ሲገባው ይህን ያላደረገው በቂ ሠራተኞች የሉኝም በሚል እንደሆነ ዶ/ር ቴዮብስታ ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡
በዚህ የተነሳ አንዳንዶቹ ዕድለኞች ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ቤተሰባዊ ምስቅልቅል መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
የሥነ ልቦና ምስቅልቅሉ እንዲሁ አልተፈጠረም፡፡
እነዚህ የዲቪ ዕድለኞቹ የፈረንጆቹ የ2022 ዲቪ አሸናፊዎች ይሁኑ እንጂ ጉዳያቸውን ማጠናቀቅ ያለባቸው በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ብቻ ነው፡፡
ባለ ዕጣዎቹ መስከረም 20/2014 ዓ.ም ጉዳያቸው ተንቀሳቅሶ እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ጥንቅቅ ብሎ መዘጋት ይኖርበታል፡፡
በዚህ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሂደቱ ካልተፈጸመ ሎቶሪው ይቃጠላል፡፡ ይህ ነው አስጨናቂ የሆነባቸው፡፡
ይሁንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አንድም የ2022 የዲቪ አሸናፊ ኢትዮጵያዊ ለቃለ ምልልስ ወደ ኤምባሲው እንዳልተጠራ ቢቢሲ ተረድቷል፡፡
ነገሩ የቅደም ተከተል ቁጥር (Case Number) ጉዳይ ነው እንዳይባል በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ ቤት የዲቪ ተራ ቁጥር ያለው ሰው እያለ ለቃለ ምልልስ ኤምባሲ አልተጋበዘም፡፡
ሆኖም በሌሎች አገሮች የቅደም ተከተል ቁጥሩ ከ40 ሺህ ቤት እልፍ ያለ ሰው እንኳ የቃለ ምልልስ ቀጠሮ እንዳገኘ ባለድሎቹ ይገልጻሉ፡፡
ነገሩ አሳሳቢ ሲሆንባቸው የዲቪ ዕድለኞቹ በማኅበራዊ መድረክ ተጠራርተው በጋራ መላ መምታት ጀመሩ፡፡
መጀመሪያ ያደረጉት ኤምባሲውን በተለያየ መንገድ መጠየቅ ሲሆን፣ የተሰጣቸው ምላሽ ከላይ ከተገለጸው የተለየ አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ኤምባሲው ይህን ሂደት የሚያሳልጡ ሠራተኞቹ ከአገር እንደለቀቁ፤ በዚህም የተነሳ አሁን ኤምባሲው ለራሱ ዜጎች ብቻ አገልግሎ እየሰጠ እንደሆነ ነው የተረዱት፡፡
ለመሆኑ አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ ይህ ሁኔታ ይቀየር ይሆን?
እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰት ኢትዮጵያ በዓለም ብቸኛዋና የመጀመርያዋ አገር ናት?
በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው በካሊፎርኒያና ዋሺንግተን ዲሲ የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጠበቃ የሆኑት አሜሪካዊውን ከርቲስ ሊ ሞሪሰንን ነው፡፡
እሳቸው ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ ለቢቢሲ እንዳስረዱት ይህ የአሜሪካ ኤምባሲ ለዕጩ የዲቪ ዕድለኞች ሰጠ የተባለው ምላሽ ውሃ የማይቋጥር ነው፡፡
ኤምባሲው በተለያየ ምክንያት ጉዳዩን ማሳለጥ ባይችል እንኳ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሌላ ኤምባሲ ማዛወር ነበረበት፡፡
ይህ ነገር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሱዳንም እንዳጋጠመ የጠቀሱት ጠበቃው፣ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ፍርድ ቤት ለማቆም እየሠሩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ጠበቃ ከርቲስ አሁን ዶ/ር ቴዮብስታን ጨምሮ 12 ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ሱዳናዊያን ከነቤተሰቦቻቸው ጥብቅና የቆሙላቸው ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ተጠያቂ የሚያደርግ ፋይል ከፍተዋል፡፡
ዋናው የክሳችን ጭብጥ ደንበኞቼ የዲቪ ጉዳያቸው በአቅራቢያ በሚገኝ ኤምባሲ በፍጥነት እንዲታይ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ እክል ገጥሞ የሚያውቀው በኢራቅ ሲሆን ጠበቃ ከርቲስና አጋሮቻቸው 25 የሚሆኑ ኢራቃዊ ዕጩ ዲቪ አሸናፊዎችንና ቤተሰባቸውን ወክለው ተከራክረዋል፡፡
ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድም ሂደቱ ጎረቤት አገር እንዲታይ አስችለዋል፡፡
ይህን ክስ ተከትሎም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአሠራር ለውጥ በማድረጉ በአፍጋኒስታን ቢሮ ጉዳያቸው ተንጠልጥሎ የነበሩ የዲቪ አሸናፊዎች በሙሉ ጉዳያቸው በፓኪስታን ኢዝላማባድ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲታይ ሆኗል ይላሉ ጠበቃ ከርቲስ፡፡
በዚህ የኢራቅ ዜጎች ጉዳይ ፍርድ ቤት ፋይል የከፈቱት በጥቅምት ወር ነበር፡፡ ጉዳዩ በጥር 5 መፍትሄ አግኝቷል፡፡
አሁንም ለኢትዮጵያዊያንና ለሱዳናዊያን ተመሳሳይ ውሳኔ እንዲመጣ እንጠብቃለን ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያዊያን ዲቪ አሸናፊዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
አሁን የኢትዮጵያዊያኑ ጉዳይ በፍርድ ቤት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንዲያስረዱ በቢቢሲ የተጠየቁት ጠበቃ ከርቲስ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ ዳኛ ተመድቦለት በሂደት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
"በኮሎምቢያ ግዛት ክስ ከፍተናል፡፡ በክሊንተን ዘመን የተሸሙት ዳኛ ኮሊን ኮላር ኮተሊ ጉዳዩን እንዲመለከቱት ተመድበዋል፡፡ በተመደቡልን ዳኛ ደስተኞች ነን፡፡"
በዓለም ላይ በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሙሉ ኃይል አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ደግሞ ከኮቪዱም በላይ የፖለቲካ ምስቅልቅ አጋጥሞ ነበር፡፡
"የውጭ ጉዳይ የዘወትር የቪዛ አገልግሎት ለመስጠት እክል ገጠመኝ ለማለት ምክንያት እንዳለው እረዳለሁ" የሚሉት ጠበቃው፣ ነገር ግን የዲቪ አሸናፊዎችን ጉዳይ ወደ ሌላ ኤምባሲ ለማዘዋወር አለመሞከሩ ነው ስሜት የማይሰጠው ነገር ይላሉ፡፡
ለመሆኑ በዲቪ ጉዳይ ፍርድ ቤት ተከራክሮ ማሸነፍ ይቻል ይሆን?
ጠበቃ ከርቲስ በዚህ ረገድ አንዳችም ጥርጥር የለውም ባይ ናቸው፡፡
"እንዲያውም በጣም ተስፋ የማደርገው በዚህ ጉዳይ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ እኛን በፍርድ ቤት ቆሞ የመከራከር ፍላጎት እንደማይኖረው ነው፡፡ ምክንያቱም የተሳሳተ ቦታ ነው የቆሙት፡፡ እኛን መሞገቱ አያዋጣቸውም፡፡ ይህንንም አሳምረው ያውቃሉ" ይላሉ፡፡
ይህ ከሆነ ታዲያ ጉዳዩን ፍርድ ቤት መውሰድ ለምን አስፈለገ?
ጠበቃ ከርቲስ ነገሩ ወደ ፍርድ ቤት መሄዱን መንግሥት ሲያውቅ በቶሎ የፖሊሲ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ፡፡
"ተስፋ የማደርገው ቶሎ የፖሊሲ ለውጥ አድርገው የኢትዮጵያ ደንበኞቼን ጉዳይ ወደ ቅርብ ኤምባሲ እንዲዘዋወር ያደርጋሉ ብዬ ነው፡፡"
የከርቲስ የጥብቅና ቢሮ አደረኩ ባለው ቅኝት በዓለም ላይ የአሜሪካ ቪዛን የሚያትሙ 200 ኤምባሲዎች ቢኖሩም፣ የዘወትር ሥራቸውን በመደበኛነት እየሠሩ ያሉት ግን 10 ብቻ ናቸው፡፡
በእርሳቸው እምነት ከአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ኮቪድ-19ኝን ተከትሎ እጅግ ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም እያሳየ ያለው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ነው፡፡
"እኔ ካሊፎርኒያ ነው ያለሁት፡፡ አዲስ አበባ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ስለማላውቅ በዚያ ላይ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ብዙም እምነት የለኝም፡፡ እስከ መስከረም 30 ድረስ ዝም ብለው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ያ ነው አስፈሪው ነገር።"
ኤምባሲውን ለምን መክሰስ አልተቻለም?
ብዙ የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶች ወረርሽኙን ተከትሎ የአሠራር ለውጥ አድርገዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ግን በዚህ ረገድ ተገቢውን ተግባር አላከናወነም የሚሉት ከርቲስ፣ ይሁንና በኤምባሲው ላይ ክስ መመሥረት አዋጪ እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡
"አንዳንዶች ለምን ኤምባሲው ሥራ እንዲጀምር አትከሱም ይሉናል፡፡ ሕጉ በዚህ ረገድ እኛን አይደግፍም፡፡ በፍጹም የሚያስኬድም አይደለም፡፡ የአሜሪካ ዳኞች በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሠራር ውስጥ ገብተው ሊወስኑ ያስቸግራቸዋል" ይላሉ፡፡
ከዚያ ይልቅ በሕግ ተመራጩ አካሄድ ዕድለኞቹ በሌላ ጎረቤት አገር ጉዳያቸው እንዲታይ ማስቻል ነው፡፡
ፍርድ ቤት የሚወስነው ውሳኔ ተፈጻሚነቱ ለሁሉም ዕድለኞች ነው?
ምንም እንኳን ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ቪዛ የማግኘት ዕድላቸው ጥያቄ ውስጥ ቢገባም ጠበቃ አቁመው የሚከራከሩት ግን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
የከርቲስ የጥብቅና ቢሮ ሱዳናዊያንን ጨምሮ ለ12 የዲቪ አሸናፊዎች ብቻ ነው የቆመው፡፡
ይህ የሆነው አንድም የጠበቃ ወጪ በመፍራት፤ አንድም ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚሆን አይደለም ብሎ በማመን፣ አንድም ተስፋ በመቁረጥ ነው፡፡
ከጠበቃ ከርቲስ ሌላ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሌላ የኢሚግሬሽን ጠበቃ ተወክለዋል፡፡
ይሁንና በለስ ቀንቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት ቢያገኝ በጠበቃ የተወከሉት ብቻ ናቸው ጉዳያቸው የሚፈጸመው ወይስ የሕጉ ተፈጻሚነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይሆናል?
ጠበቃ ከርቲስ ይህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ የለውም ይላሉ፡፡
"ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበሩ ሁኔታዎች ዳኞች በእኛ ለተወከሉ ደንበኞች ብቻ መፍትሄ ሰጥተው ያውቃሉ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሁሉንም የሚያካትት ውሳኔ ተሰጥቶ ያውቃል፡፡"
በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ጥብቅና የቆሙላቸውን የ25 ኢራቃዊያንና ቤተሰባቸውን ጉዳይ ነው፡፡
"እኛ ጥብቅና የቆምንላቸው ለ25ቱ ኢራቃዊያን ቢሆንም ክሱን ተከትሎ የተደረገው ለውጥ ግን ለሁሉም ኢራቃዊና አፍጋኒስታናዊያን ጭምር ተፈጸሚ ሆኗል፡፡"
ኢትዮጵያዊያኑ ለደረሰባቸው እንግልት ለምን የአሜሪካ መንግሥትን ካሳ አይጠይቁም?
ጠበቃ ከርቲስ በዲቪ ዕድለኞች ላይ ሊደርስ የሚችለው ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ቀላል እንደማይሆን ይረዳሉ፡፡
ይሁንና አሁን አጀንዳው ካሳ አይደለም፡፡
"የእኛ ክስ ዋናው ማጠንጠኛ ጉዳያቸው በሌላ ኤምባሲ እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ዋናው ጉዳይ ቪዛ እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ የካሳ ጉዳይ ተገቢ ጥያቄ ቢሆንም አሁን ጊዜው አይደለም፡፡"
ቪዛ የማግኘቱ ጉዳይ መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ ሲያብራሩም፣ ኮንግረስ በዓመት ወደ 50 ሺህ ቪዛ እንዲያትሙ የፈቀደ ቢሆንም፤ ኤምባሲዎች አሁን እየሄዱ ያሉበት ፍጥነት 6 ሺህ ቪዛ እንኳ ለመስጠት የሚያስችል አይደለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ይህን ለመለወጥ ወደፊት የቡድን ክስ መክፈታችን አይቀርም ብለዋል ጠበቃ ከርቲስ፡፡
የዲቪ ዕድለኞቹ ቁርጣቸውን እስከመቼ ያውቃሉ?
የ12 ኢትዮጵያዊያንና ሱዳናዊያንን ጉዳይ የያዙት ጠበቃ ከርቲስ ይህ ጉዳይ ፍሬ እንደሚያፈራ አይጠራጠሩም፡፡
"እንዲያውም ዳኛዋ ጉዳዩን መመልከት ሳይጀምሩ ውጭ ጉዳይ የፖሊሲ ማስተካካያው ያደርጋል ብዬ ነው የምጠብቀው፡፡ ገና ክስ መከፈቱን ሲሰሙ የዕጩዎች ጉዳይ በሌላ አገር ይታይ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ሕጉ እኛን ነው የሚደግፈን" ብለዋል፡፡
በእርግጥ ክስ ሲከፈት መንግሥት ምላሽ መስጠት ያለበት በ60 ቀናት ነው፡፡
ጠበቃ ከርቲስ ግን ይህን ሁሉ ጊዜም ላይወስድ እንደሚችል ነው ተስፋ የሚያደርጉት፡፡
"ከ60 ቀን በፊት ውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ይቀይራሉ፤ እንጂ እኛን ፍርድ ቤት ቆመው አይሞግቱንም፡፡"
ዲቪ 2022: 'እያነቡ እስክስታ'
ዶ/ር ቲዮብስታ ውጭ ባሉ ዘመዶች እርዳታ ጠበቃ ማቆም ብትችልም ሌሎች 2 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ግን አሁንም የኤምባሲውን ዓይን ለማየት ሽሮ ሜዳ ድረስ ከመመላለስ ውጭ ተስፋቸው እየተሟጠጠ ነው፡፡
ጠበቃ ማቆም የቻሉትም ቅድመ ክፍያ ነው የፈጸሙት፡፡ ነገሩ ከተሳካ በኋላ ደግሞ አሜሪካን ሲረግጡ ቀሪ ዕዳቸውን ለመክፈል ተስማምተዋል፡፡
ጠበቃ ከርቲስ ከዚህ ቀደም ካላቸው የኢሚግሬሽን ጥብቅና የሥራ ቆይታ ተነስተው ኢትዮጵያዊያን ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላም ቢሆን በታማኝነት ያለባቸውን ክፍያ በመክፈል መልካም ስም ያላቸው ናቸው ይላሉ፡፡
ይህን የሚሉት በ2020 እና በ2021 በትራምፕ አስተዳደር የተጣሉ መልክ ብዙ ዕቀባዎች የተነሳ ብዙ የዲቪና ኢሚግሬሽን ተመሳሳይ ጉዳዮችን ይዘው ጥብቅና የቆሙላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ዋቢ አድርገው ነው፡፡
ዶ/ር ቲዮብስታ የሚያሳስባት ግን ወደፊት የሚጠብቃት የጠበቃ ክፍያ አይደለም፡፡ ለዓመታት ያለመችው ሕልሟ ከእሷ ቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ እንዳይጨናገፍ ነው፡፡
ዲቪ ያመጣላትን የትምህርት ዕድል በፍጹም ማጣት አትፈልግም፡፡
"ዲቪ በሕይወት አንድ ጊዜ የሚገኝ ዕድል ነው፡፡ እዚያ ሄጄ የላቀ ሕክምና ትምህርት መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ለጊዜው ምንም ማሰብ አልፈልግም" ትላለች፡፡
ይሰምርላት ይሆን?