ፈረንሳይ እና አጋሮቿ ጦራቸውን ከማሊ ሊያስወጡ መሆኑን ማክሮን አስታወቁ

ታትሟል

ፈረንሳይ እና አውሮፓውያኑ አጋሮቿ ጥምር ጦራቸውን ከማሊ ሊያስወጡ መሆኑን ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታወቁ።

ባለፉት 10 ዓመታት ጥምር ጦሩ በማሊ ጽንፈኛ እስለማዊ ታጣቂዎችን ሲዋጉ ቆይተዋል።

ማክሮን ጥምር ጦሩን ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ማስወጣት ግድ የሆነው በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዘው የማሊ ጁንታ ወታደራዊ መንግሥት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በመሻከራቸው ነው ብለዋል።

ጥምሩ ጦሩ በሌላ በሳህል ቀጠና ውስጥ በሚገኝ አገር ይሰማራል ተብሏል።

ማክሮን ከፓሪስ በሰጡት መግለጫ፤ "ድብቅ ዓላማውን ከማንጋራው" መንግሥት ጋር ወታደራዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም ብለዋል።

በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዴንማርክ በማሊ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ጦሯን ከማሊ ማስወጣት እንደምትጀምር ማስታወቋ ይታወሳል።

ዴንማርክ ጦሯን ከማሊ ለማስወጣት የወሰነችው የሽግግር መንግሥቱን ጥያቄ ተከትሎ ነው። የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ጥምር ኃይሎች የዴንማርክ ጦር በማሊ እንዲቆይ የማሊን የሽግግር መንግሥት ሲወተውቱ ነበር።

ማክሮን በመግለጫቸው በቀጠናው ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸው፤ ኒጀር ከማሊ የሚወጣውን የተወሰነ ጦር ለመቀበል ተስማምታለች ብለዋል።

ፈረንሳይ 5ሺህ ወታደሮቿን በቀጠናው ያሰማራች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ገሚሱ በማሊ ባሉ ሦስት ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። ማክሮን ወታደሮቻቸውን ከ4 እስከ 6 ወራት ውስጥ አስወጥተው እንደሚጨርሱ ተናግረዋል።

በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የማሊ እና ፈረንሳይ ግንኙነት እጅጉን ተቀዛቅዟል።

ከጥቂት ወራት በፊት ምዕራባውያን አገራት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማሊ መሰማራታቸውን አስታውቀው ነበር።

ይህ መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገ ዋግነር ግሩፕ የተሰኘ የቅጥረኛ ወታደሮች ስብስብ ከዚህ ቀደም በሶሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ተሰማርቶ እንደነበረ ተዘግቧል።

ማክሮን ይህ ቡድን የራሱን እና የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ነው ማሊ የገባው ሲሉ ኮንነዋል።

የፈረንሳይ እና አጋር ጦር አባላት ከማሊ መውጣታቸው በአገሪቱ እና በቀጠናው የደኅንነት ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።