በሕንድ 13 የሠርግ ታዳሚዎች ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸው አለፈ

ታትሟል

ሕንድ ውስጥ በአንድ ሠርግ ላይ ከታደሙ ሰዎች መካከል 13ቱ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸው አለፈ።

በሰሜናዊ ሕንድ በምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ባጋጠመው አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸው ተገልጿል።

ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ 13ቱ የሠርጉ ታዳሚዎች ከውሃ ጉድጓዱ አናት ላይ በተሰራ የብረት አግዳሚ ላይ ተቀምጠው ነበር። ይሁን እንጂ የብረት አግዳሚው የሰዎቹን ክብደት መያዝ ባለመቻሉ ሴቶች እና ሕጻናቱ ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸው አልፏል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ 2 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወደሳቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ክስተቱን አሳዛኝ ብለውታል።

ይህ አደጋ ያጋጠመው ረቡዕ ምሽት 'ሃልዲ' የተሰኘ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እየተከናወነ ሳለ ነበር።

አደጋው ካጋጠመ በኋላ በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ተጎጂዎቹን በፍጥነት ወደ የሕክምና ተቋም ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም 11ዱ ወዲህ አደጋው ባጋጠመበት ቦታ ሕይወታቸው አልፏል።

የግዛቷ አስተዳዳሪ የተጎጂ ቤተሰቦችን ድጋፍ እንዲያገኙ በኡታር ፕራዴሽ ግዛት ለሚገኙ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።