ቢቢሲ ኢራን በጋዜጠኞቹ ላይ የምታደርሰውን ትንኮሳ አስመልክቶ ለተመድ ቅሬታ አስገባ

የቢቢሲ ፐርዢያን አገልግሎት
ታትሟል

ቢቢሲ በፋርሲ ቋንቋ በሚያቀርበው የቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎቱ ላይ በሚሰሩ ጋዜጠኞች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ኢራን ተከታታይ ትንኮሳ እየፈጸመች ነው ሲል ቅሬታውን ለተባበሩት መንግሥታት አገልግሎት ድርጅት አስገብቷል።

ኢራን በውጭ በሚኖሩ ጋዜጠኞች ላይ ህገወጥ ተግባራትን እያከናወነች ነው የሚል ክስ ከአንድ አመት በፊት የቀረበባት ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የጸጥታ ስጋቶች እየተባባሱም መጥተዋል።

አለም አቀፉ የቢቢሲ አገልግሎት ዳይሬክተር ሊሊያን ላንዶር እንደተናገሩት ሰራተኞቻቸው የገንዘብና የንብረት እገዳ፣ በኢንተርኔት ላይ ትንኮሳ እና የግድያ ዛቻዎችና ማስፈፈሪያዎች ገጥሟቸዋል።

"ትንኮሳው መቆም አለበት" ሲሉም በኢስቶኒያ በነበረ የሚዲያ ነፃነት ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

የኢራን መንግሥት ከዚህ ቀደም ውንጀላውን ያስተባበለ ሲሆን ቢቢሲንም የሃሰት መረጃ በማሰራጨትና የኢራን መንግሥት ከስልጣን ለማውረድ ይሰራልም ሲል ከሷል።

የቢቢሲ ፐርዢያን አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳሚዎች ያሉት ሲሆን አገልግሎቱ በታገደበትም ኢራን 13 ሚሊዮን ታዳሚዎችን ይደርሳል።

ኢራን በቢሲ ፐርዢያን ጋዜጠኞችና ቤተሰቦቻቸው ላይ በማነጣጠር ከአስር አመት በላይ ትንኮሳ ፈፅማለች ብሏል መግለጫው።

ጋዜጠኞች እስርን በመፍራት ወደ አገራቸው ኢራን መመለስ ያልቻሉ ሲሆን በቤተሰቦቻቸው ላይ የጉዞ እገዳ መጣልን ጨምሮ በዘፈቀደ መታሰርን ጨምሮ ምርመራ ተደርጎባቸዋል ብሏል።

ቢቢሲ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስገባው ቅሬታ ለአመታት የቀጠለውንና እንደ አዲስ በጋዜጠኞቹ ላይ የቀጠለውን ትንኮሳ አስመልክቶ ነው።

ለተመድ የገባውም ቅሬታ የሚከተሉትን ሃሳቦች አካቷል፦

  • በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት ተቀማጭ የሆኑ የቢቢሲ ኒውስ ፐርዢያን ጋዜጠኞች የደህንነት ስጋቶች መጨመር
  • · በኢራን ውስጥ በቤተሰብ አባላት ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ መጨመር
  • · በጋዜጠኞች እና በቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ላይ እንደ ቅጣት የተጫነው የንብረት እገዳ ከፍተኛ ጫና መሆንና ሌሎችም ይገኙበታል።