የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ በግቢው ዶክተር ለደረሰው ወሲባዊ ጥቃት 250 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

የማህጸኑ ሃኪም ዶክተር ጄምስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በግቢው የማህፀን ሐኪም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ላሉ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎች 250 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

በርካታ ሴት ተማሪዎች በሎስ አንጀለስ የሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ (ዩሲኤልኤ) ጄምስ ሂፕስ የተባለውን ዶክተር በታካሚዎች ላይ ያደረሰውን የወሲብ ጥቃት ሆን ብሎ ለመደበቅ ሞክሯል ሲሉ ይከሳሉ።

ጄምስ ሂፕስ በዩሲኤልኤ የጤና ማዕከል ለ35 አመታት ያህል ከአውሮፓውያኑ 1983 እስከ 2018 ድረስ አገልግለዋል።

የካንሰር ህመም ያለባቸውን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ዶክተሩ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ዩኒቨርስቲ እስከ አውሮፓውያኑ 2017 ድረስ በዶክተሩ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መመርመር አልጀመረም።

ዩኒቨርስቲውም የማህጸን ሃኪሙ በታካሚዎች ላይ ያደረሰውን ወሲባዊ ጥቃት ሆን ብሎ በመደበቅ በሚል በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሶች ቀርበውበታል።

የዶክተሩም የህክምና ፈቃድ በአውሮፓውያኑ 2019 በአንድ ዳኛ እንዲታገድ ተደርጓል።

ዩኒቨርስቲው ይህ የገንዘብ ስምምነት ጥቃት ለደረሰባቸው ተማሪዎች ፈውስና ህመማቸውም መቋጫ እንደሚሆናቸው ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ዶክተሩ ሰባት ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም በ21 ክሶች የቀረበበት ሲሆን ለሁሉም ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

"በጄምስ ተፈጽሟል የተባለው ድርጊጠዕ አጸያፊ እና ከዩኒቨርሲቲው እሴቶች ጋር የሚጻረር ነው" በማለት ዩሲኤልኤ ማክሰኞ እለት መግለጫ አውጥቷል ።

"የእኛ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ግዴታ ምንጊዜም ለምናገለግላቸው ማህበረሰቦች ይሆናል፣ እናም ይህ የገንዘብ ስምምነት ለተጎጅዎች ፈውስ እና ለህመማቸውም መቋጫ አንድ እርምጃ ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን።" ብሏል።

ነገር ግን ካራ ካግል የተባለች ግለሰብ የካንሰር ታማሚ በነበረችበት ወቅት በዶክተሩ ጥቃት የደረሰባት ሲሆን ለሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደተናገረችውም "ዛሬ ከስምንት ረጅም አመታት በኋላ ለደረሰብኝ ጥቃት ምላሽ አገኘሁ" ብላለች።

"በዚህ ውሳኔ ውስጥ የተወሰነ ማጽናኛ ቢኖርም፣ ዩኒቨርስቲው በዶክተሩ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት በጥቃቱ ለተሰቃዩ ሴቶች በሙሉ ልቤ ተሰብሯል" ብላለች

ማክሰኞ እለት የተደረሰው ስምምነት ከ300 በላይ ታካሚዎች ያቀረቡትን ክስ አያቆመውም።

ባለፈው ሀምሌ ወር የአሜሪካ ፌደራል ዳኛ ዶክተር ጄምስ 73ሚሊየን ዶላር ገንዘብ እንዲከፍል አዞ ነበር፣ ይህም ከ5,500 በላይ ሴት ተማሪዎች ያቀረቡትን ውንጀላ ተከትሎ ነበር።

ክሱን የያዙት ጠበቆች እንደሚሉት ዶክተር ጄምስ በአንድ ወቅት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው የህክምና ባለሙያ ነበሩ።