በዩክሬን ውጥረት ምክንያት አሜሪካ በአውሮፓ ያሉ ወታደሮቿን ቁጥር ከፍ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ልትፈፅም ትችላለች በሚል ስጋት በዚህ ሳምንት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አውሮፓ እንደሚልኩ ፔንታጎን አስታውቋል።
ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ከሰሜን ካሮላይ ግዛቷ ፎርት ብራግ፣ ወደ ፖላንድ እና ጀርመን የሚላኩ ሲሆን በጀርመን ያሉ ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮች ወደ ሮማኒያ ይላካሉ።
ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ምንም አይነት እቅድ እንደሌላት ብታስተባብልም 100 ሺህ የሚገመተውን ሰራዊቷን በዩክሬን ድንበር አካባቢ አሰማርታለች።
ሩሲያ አሜሪካ ወታደሮች ማሰማራቷን "አጥፊ" ስትል ጠርታዋለች።
ሩሲያ የዩክሬንን ደቡባዊ ክሪሚያ ፔኒንሱላን ወደ ግዛቷ ያስገባችው ከስምንት አመታት በፊት ሲሆን በምስራቅ ዶንባስ ግዛት የተነሳውን ደም አፋሳሽ አመፅም መደገፏን ተከትሎም በሁለቱ አገራት ውጥረት እንደነገሰ ነው።
ሞስኮ የዩክሬን መንግሥት የሚንስክን ስምምነትን ተግባራዊ አላደረገችም ስትል ትከሳለች።
በሩሲያ የሚደገፉ አማፂያን ሰፊ ግዛት ተቆጣጥረው ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ቢያንስ 14 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።
ይህንንም ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭና በምስራቅም ሰላም እንዲሰፍን በሚል በሩሲያና በዩክሬን በኩል አለም አቀፍ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በአውሮፓ የሚሰማራው የአሜሪካ ጦር በዩክሬን በቀጥታ በጦርነቱ ተሳታፊ ባይሆንም ለአሜሪካ አጋሮች ድጋፍን ይሰጣል።
አሁን አሜሪካ በአውሮፓ እያደረገች ያለችው የጦር ስምሪት ባለፈው ወር ፔንታጎን ካስፈለገ ወደ አውሮፓ ለማሰማራት ዝግጁ እንዲሆኑ ካስጠነቀቀው 8 ሺህ 500 ወታደሮች በተጨማሪ ነው።
"ለፑቲን እንዲሁም እውነቱን ለመናገር ለአለም ኔቶ [የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት] ለአሜሪካም ሆነ ለአጋሮቻችን ከፍተኛ ስፍራ ያለው ነው የሚለውን ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው" በማለት የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።












