በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ የሶሪያ ሕጻናት በከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ

ስደተኞች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች
ታትሟል

በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በጣለው በረዶ እና ይህን ተከትሎ በተፈጠረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩት ሁለት ጨቅላዎች ሕይወታቸው አለፈ።

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ በቅዝቃዜው ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው የ7 ቀናት እና የሁለት ወራት ጨቅላ ሕጻናት ናቸው።

ወደ 2.8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያዊያን በኢድሊብ ግዛት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

አብዛኛዎቹ ሙቀት ሰጪ ልብሶች እና ማሞቂያ ሳይናራቸው ባረጁ ድንኳኖች ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ።

ለአስር ዓመታት በዘለቀው የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች ከየትኛው ጊዜ በላይ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተመድ አሳስቧል። በሶሪያ የተከሰተው የምጣኔ ሃብት ቀውስ በአንድ ዓመት ውስጥ የምግብ ዋጋ በእጥፍ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን እና ለሶሪያውያን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መቀነሱን ድርጅቱ አስታውቋል።

ከሁለቱ ጨቅላዎች ሞት በተጨማሪ ከአንድ ሳምንት በፊት በአሌፖ ግዛት ውስጥ በሚገኝ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖር የነበረ ሌላ የአንድ ወር ጨቅላ በቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ የሶሪያ በጎ አድራጊ ድርጅት አስታውቋል።

ሌላ ታዳጊ ደግሞ ተጠልሎበት የነበረውን ድንኳን በተከማቸ በረዶ ከፈረሰ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

እንደ ተመድ ከሆነ በኢድሊብ እና አሌፖ የሚገኙ 287 መጠለያ ጣቢያዎች በከፍተኛ ቅዝቃዜ፣ በጎርፍ እና በኃይለኛ ንፋስ ተመተዋል። በዚህም ከ935 በላይ መጠለያ ድንኳኖች ወድመዋል።

የሶሪያ የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ሶኒዓ ካሁሽ ሕጻናት በቅዝቃዜ ምክንየት ሕይወታቸው ለአደጋ መጋለጥ የለበትም ይላሉ።

ዳይሬክተሯ ከ11 ዓመታት በፊት በሶሪያ በተቀስቀሰው ቀውስ ምክንያት እየማቀቁ ያሉ ሕጻናትን የዓለም ማሕብረሰብ የዘነጋቸው ይመስላል ብለዋል።