አምነስቲ እስራኤልን 'የአፓርታይድ' አገር ሲል ወቀሰ

ታትሟል

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስራኤልን 'የአፓርታይድ አገር' ሲል ገለጻት።

አምነስቲ በእስራኤል ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንና እስራኤል በወረራ የያዘቻቸው ግዛቶች የተመለከቱ የእስራኤል ሕግጋቶች፣ ፖሊሲዎች እና ትግበራዎች ከአፓርታይድ (ከመድልዎ) ሥርዓት ጋር የሚስተካከል ነው ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አዲስ ባወጣው ሪፖርቱ የእስራኤል መንግሥት ለአይሁዳዊያን ጥቅም ሲል በተቋማዊ አሰራሩ የፍልስጤም ሕዝብን በጭቆና ይገዛል ብሏል።

አፓርታይድ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የዘር መድልዎ ፖሊስ ነበር። ይህ ፖሊሲ በደቡብ አፍሪካ እአአ ከ1948 እስከ 1991 ሲተገበር ቆይቷል።

ይህ ፖሊሲ አናሳ በሆኑት በነጭ በተሞላ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በብዙሃኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ላይ የተጫነ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አፓርታይድ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ተደርጎ ይቆጠራል።

እስራኤል የአምነስቲን ሪፖርት መሠረተ ቢስ ስትል አመርራ ተቃውማለች። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሪፖርቱን፤ "ሐሰት፣ ያልተጣጣመ፣ መሠረተ ቢስ እና እስራኤል ጠል ከሆነ ተቋም የወጣ" ብለውታል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ የወጣው መግለጫ፤ የአምነስቲ ሪፖርት የእራኤልን እና የአይሁድ ሕዝብን የመኖር መብት የማይቀበል ታሪካዊ ዳራን ከግምት ያላስገባ ሲል በጠንካራ ቃላት አጣጥሎታል።

በሌላ በኩል የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱን በመልካም ጎኑ እንደሚቀበለው ገልጿል።

የፍልስጤም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱ የእስራኤልን፤ "ዘረኝነት፣ አድልዎ፣ ጭቆና፣ ቅኝ ግዛት እና አፓርታይድ" ማረጋገጫ ነው ብሎታል።

በደቡብ አፍሪካ ተተግብሮ በነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት ጥቁሮች አናሳ ተደርገው ይቆጠራሉ። በብሔራዊ ምርጫዎች ላይ ጥቁሮች ድምጽ አይሰጡም፤ በበርካታ የደቡብ አፍሪካ አካባቢዎችም መሬት እንዲኖራቸው አይፈቀድም። ክህሎት የሚጠይቁ ሥራዎች ነጮች ብቻ እንዲሰሩ ያስገድዳል።

ይህ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ ኔልሰን ማንዴላ እአአ 1994 ላይ የመጀመሪያው ጥቁር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት በመሆን መመረጣቻው ይታወቃል።

ከእስራኤል 9.45 ሚሊዮን ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆኑት አረቦች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ እራሳቸውን እንደ ፍልስጤማዊ አድርገው ይቆጥራሉ። 2.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና በምሥራቅ እየሩሳሌም ይኖራሉ።

1.9 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ደግሞ በጋዛ ሰርጥ ይኖራሉ። አብዛኛው ፍልስጤማዊያን ግን በፍልስጤም አስተዳደር ስር በሚተዳደረው ዌስት ባንክ የሚኖሩ ሲሆን፤ በጋዛ የሚኖሩት ደግሞ በሃማስ አስተዳደር ስር ይገኛሉ።

ከ600ሺህ በላይ አይሁዳውያን በዌሰት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌም 140 በሚሆኑ የሰፈራ ቦታዎች ይኖራሉ። ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ይህን የእስራኤል የሰፈራ ቦታዎች ሕገ-ወጥ አድርጎ ይመለከተዋል።

እስራኤል ሁሉም ዜጎቼ በሃይማኖት እና በዘር ሳይለያዩ እኩል መብት ነው ያላቸው ብትልም፤ አምነስቲ ግን በእስራኤል የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ከአይሁዳውያን ያነሱ ተደርገው ይቆጠራሉ ብሏል በሪፖርቱ።