በፕሪሚየር ሊጉ የጥር ወር የዝውውር መስኮት ማን ማንን አስፈረመ?

ታትሟል

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የጥር ወር የዝውውር መስኮት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት እኩለ ለሊት ላይ ተጠናቋል።

ከዚህ በታች የትኞቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ማንን አስፈረሙ የሚለውን እንመለከታለን።

ኒውካስትል ዩናይትድ

ለጥቂት ሳምንታት በቆየው የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቀዳሚ ስፍራን የሚይዘው ኒውካስትል ነው።

ኒውካስትል ብሩኖ ጉዊማሬዝን ጨምሮ ስመ ጥር እግር ኳሰኞችን በዚህ የጥር ወር የዝውውር መስኮት መያዝ ችሏል።

ብሩኖ ጉዊማሬዝን ከፈረንሳዩ ሊዮን በ35 ሚሊዮን ፓዎንድ ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ አምርቷል።

ኒው ካስትል የግራ መስመር ተመላላሹን ማት ታርጌት ከአስተን ቪላ በውሰት ወስዷል። የ26 ዓመቱ ታርጌት እስከ የውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ በሴንት ጀምስ ፓርክ የሚቆይ ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪም ኒውካስትል ዳን በርን ከብራይተን በ13 ሚሊዮን ፓውንድ በማስፈረም የተከላካይ መስመሩን አጠናክሯል።

ክሪስ ውድ ከበርንሊ ወደ ኒውካስትል በ25 ሚሊዮን ፓውንድ ተዘዋውሯል።

በጥሩ የዝውውር መስኮት ኒውካስትልን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል ብዙ ልምድ ያለው የ31 ዓመቱ ተከላካይ ኪረን ትሪፒየር ይገኝበታል።

ቲሪፒየር እስከ ቀጣይ ዓመት የውድድር ዘመን ማብቂያ ድረስ በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ኒውካስትልን ተቀላቅሏል።

ኤቨርተን

ፍራንክ ላምፓርድን አሰልጣኙ አድርጎ የቀጠረው የመርሲሳይዱ ክለብ ኤቨርተን በዚህ የዝውውር መስኮት ብዙ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ ክለቦች መካከል አንዱ ነው።

የኤቨርተን የጥር ወር ትልቁ ፈራሚ የቶተንሃም ተጫዋች የነበረው ዴሊ አሊ ነው። ዴሊ አሊ እስከ 40 ሚሊዮን ፓውንድ ሊደርስ በሚችል ወጪ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ወደ ሊቨርፑል ከተማ መጥቷል።

ኤቨርተን ቢሊ ክሬሊን ከፍሊትዉድ ታውን ይፋ ባልተደረገ መጠን አዘዋውሯል።

ሌላው የኤቨርተን የጥር ወር ትልቁ ፈራሚ የማንችስተር ዩናይትዱ ዶኒ ቫን ደ ቢክ ነው። በኦልትራፎርድ በቂ የጨዋታ ጊዜን እያሳለፈ ያልነበረው አማካዩ ቫን ደ ቢክ በውሰት ወደ ኤቨርተን አቅንቷል።

ኤቨርተን የአስተን ቪላውን አንዋር ኤል ጋዚን በውሰት ሲወስድ ከሬንጀርስ ደግሞ የቀኝ ተመላላሹ ናታን ፒተርሰንን በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ለአምስት ዓመታት አስፈርሟል።

ሊቨርፑል

ሌላኛው የመርሲሳይድ ክለብ ሊቨርፑል ሉዊዝ ዲያዝን ከፖርቶ አስመጥቷል።

ክሎፕ ለኮሎምቢያዊው የክንፍ ተጫዋች 37 ሚሊዮን ፓውንድ በመክፈል ለቀጣይ አምስት ዓመታት አስፈርመውታል።

ቶተንሃም

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ንዶምብሌን አሰናብቶ ሁለት የጁቬንቱስ ተጫዋቾችን ወደ ሰሜን ለንደን አምጥቷል።

የኡራጋዩ አማካይ ሮድሪጎ ቤንታንኩር ለቀጣይ 4 ዓመታት በሰሜን ለንደኑ ክለብ ለመቆየት ውል ያኖረ ሲሆን፤ የስዊድኑ የክንፍ ተጫዋች ዴጃን ኩሉሴቪስኪ ለ18 ወራት በውሰት ቶተንሃምን ተቀላቅሏል።

በሌላ በኩል ቶተንሃም ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ያስፈረመውን ንዶምብሌን በውሰት ለሊዮን ሰጥቷል። አርጀንቲናዊው ጂኦቫኒ ሎ ሴልሶ ቪላሪያን እንዲሁም የ20 ዓመቱ ታዳጊ ብራያን ጊል ቫሌንሺያን እስከ ውድድሩ ዘመኑ መጠናቀቂያ በውሰት ተቀላቅለዋል።

አስተን ቪላ

ሉካስ ዲኘ ከኤቨርተን ወደ ቪላ በ25 ሚሊዮን ፓዎንድ ተዘዋውሯል።

የፈረንሳዩ የግራ መስመር ተጫዋች በኤቨርተን ቆይታው ተመራጭ ሳይሆን በመቅረቱ ክለቡ እንዲለቀው ጥያቄ አቅርቦ ነበር ተብሏል።

የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረው የስቲቨን ጄራርድ ፈራሚ ብራዚላዊው ፊሊፔ ኩቲኒዮ ነው። ኩቲንሆ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ከባርሴሎና በውሰት ወደ ቪላ መጥቷል።

ቪላዎች የአርሰናሉን ተከላካይ ካለም ቻምበርስን በነጻ ወስደዋል።

ስዊዲናዊው ግብ ጠባቂ ሮቢን ኦሴን ከጣሊያኑ ሮማ አስንተን ቪላን በውሰት ተቀላቅሏል።

ማንችስተር ሲቲ

የፕሪሚየር ሊጉን ሰንጠረዥ በሰፊ የነጥብ ልዩነት እየመሩ የሚገኙት ሲቲዎች አርጀንቲናዊውን የፊት መስመር ተጫዋች ለአምስት ዓመታት አስፈርመዋል።

ከሪቨር ፕሌት ሲቲን የተቀላቀለው ጁሊያን አልቫሬዝ እስከ ሐምሌ ድረስ በክለቡ ይቆያል።

ብሬንትፎርድ

የክርስቲያን ኤሪክሰን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለስ የበርካቶችን ልብ በደስታ ያሞቀ ይመስላል።

የቀድሞ የቶተንሃም ተጫዋች በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር አገሩን ዴንማርክን ወክሎ እየተጫወተ ሳለ በልብ ሕመም ተዝለፍልፎ ሜዳ ላይ ወድቆ እንደነበረ ይታወሳል።

የ29 ዓመቱ ኤሪክሰን በአውሮፓ ዋንጫ ላይ ካጋጠመው ክስተት በኋላ እግር ኳስ ባይጫወትም፤ ብሬንትፎርድ ለስድስት ወራት አስፈርመውታል

በተመሳሳይ አርሰናል በርካታ ተጫዋቾቹን ከኤሜሬትስ አሰናብቶ፤ ለአሁናዊ ችግሩ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አዲስ ተጫዋች ወደ ኤሜሬትስ ማምጣት ተስኖታል።

የሚኬል አርቴታው አርሰናል፤ ጎል አዳኙን ፒዬር ኦባሚያንግ በነጻ ለባርሴሎና አሳልፎ ሰጥቶ ተተኪውን አጥቂ ማስፈረም ሳይችል የውድድር መስኮቱ ተዘግቷል።