የሁለት አስረኞች መገደልን ተከትሎ በአሜሪካ እስር ቤቶች የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Federal Bureau of Prisons
አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ አንድ አስር ቤት የተከሰተን የቡድን ፀብ ተከትሎ ሁለት አስረኞች ከተገደሉ በኋላ ሁሉም የአሜሪካ ፌደራል አስር ቤቶች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ።
የፌደራል እስር ቤቶችን የሚቆጣጠረው ተቋም እንዳለው ጠንካራ ጥበቃ በሚደረግለት ቢዩሞንት አስር ቤት ውስጥ ሰኞ ዕለት በተከሰተው ፀብ ከሞቱት በተጨማሪ ሁለት እስረኞች ክፉኛ የቆሰሉ ሲሆን ጊዜያዊ የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው ለጥንቃቄ ሲባል ነው ብሏል።
በአንድ እስር ቤት የተከሰተን ችግር ተከትሎ በአጠቃላዩ የፌደራል መንግሥቱ እስር ቤቶች ላይ እንዲህ አይነቱን እርምጃ መውሰድ የተለመደ አይደለም ተብሏል።
በቅርብ ጊዜ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በመላዋ አሜሪካ በፌደራል መንግሥቱ የሚተዳደሩ ከ150 ሺህ በላይ አስረኞችን የያዙ 134 እስር ቤቶች ይገኛሉ። ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ አብዛኞቹ አስረኞች የሚገኙት በግዛቶች ስር በሚተዳደሩ እስር ቤቶች ውስጥ ነው።
በእስር ቤቶች ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጣል እስረኞች ከክፍላቸው እንዳይወጡ የሚደረግ ሲሆን ጠያቂዎችም እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።
እርምጃውን ተከትሎ በተሰጠው መግለጫ ክልከላው ለአጭር ጊዜ የሚቆይና "ለፀጥታና ለደኅንነት" ሲባል የተወሰደ ከመሆኑ ውጪ ዝርዝር አልተሰጠም።
ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ግጭት በቴክሳስ 1,372 እስረኞች በያዘው የቢዩሞንት እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው ሎስ አንጀለስ እና ኤል ሳልቫዶር ውስጥ ጭምር የሚንቀሳቀሰው በጭካኔ ድርጊቶች የሚታወቀው ኤምኤስ-13 የተባለው የወሮበሎች ቡድን የተሳተፈበት ነው።
አሶሺየትድ ፕሬስ ለውሳኔው ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደተረዳው በአስረኞቹ መካከል የተከሰተውን ፀብ ተከትሎ በሌሎች እርስ ቤቶች ውስጥም የበቀል እርምጃ እንዳይስፋፋ የተላለፈ ውሳኔ ነው ብለዋል።
በፀቡ የተገደሉት አስረኞች በከባድ ወንጀል የተፈረደባቸው 'የሚክሲኮ ማፊያ' የተባለው የወሮበላ ቡድን አባላት ናቸው። በፀቡ በእስር ቤቱ ሠራተኞች ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተነግሯል።
ይህ የሜክሲኮ ማፊያ ቡድን በአሜሪካ አስር ቤቶች ውስጥ አስከ 300 የሚደርሱ አባላት ያሉት ሲሆን፣ እንደ ኤፍቢአይ መረጃ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ኃያላን ሲሆኑ በዕፅ ዝውውርና በሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሳታፊ እንደሆኑ ይነገራል።
ተቀናቃኙ ሌላኛው የወሮበሎች ቡድን ኤምኤስ-13 በኤል ሳልቫዶር ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረውን አሰቃቂ የእርስበርስ ጦርነት ሸሽተው በመጡ ስደተኞች የተመሰረተ ሲሆን ጭካኔ በተሞላበት ድርጊታቸው ይታወቃሉ።
በኤፍቢአይ ግምት መሠረት ይህ ቡድን አስከ 10,000 የሚደርሱ አባላት በአሜሪካ ውስጥ ያሉት ሲሆን ይህም በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ግዙፍ የወንጀለኛ ቡድኖች መካከል አንዱ ያደርገዋል።












