አሜሪካና ሩሲያ በተመድ ስብሰባ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ተፋጠጡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ላይ ከፍተኛ ሰራዊት ማስፈሯን ተከትሎ በተጠራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በአሜሪካና በሩሲያ ልዑካን መካከል ቁጣና ንዴት የተሞላበት ፍጥጫ እንደነበር ተገልጿል።

ይህንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ የጠራችው አሜሪካ ናት።

በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ሩሲያ በድንበር ላይ እያደረገችው ያለው የጦር ስምሪት በአውሮፓ በአስርት አመታት ውስጥ ከታየው ትልቁ ነው ብለዋል።

የሩሲያ አቻቸው በበኩላቸው አሜሪካ የማያስፈልግ ውዥንብር እየፈጠረች ነው በሩሲያ ጉዳዮች ላይ ተቀባይነት የሌለው ጣልቃ ገብነት እያደረገች ነው ሲሉ ከሰዋታል።

ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ ተጨማሪ ማዕቀብ እንጥላለን ሲሉ አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግድም ቃል ገብተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ለክሬምሊን ቅርብ ከሆኑ ግለሰቦች እና ንግዶች ባለፈ መልኩ ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ላይ የሚያነጣጥር ህግ እየተዘጋጀ ነው።

የአሜሪካ ባለስልጣን በበኩላቸው ለክሬምሬሊን ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች ከአለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት እንዲቆራረጡ የሚያደርግ ማዕቀብ ይጣላል ብለዋል።

ሩሲያ 100 ሺህ የሚገመቱ ወታደሮች፣ ታንኮች፣ መድፍ እና ሚሳኤሎችን በዩክሬን ድንበር አካባቢ አስፍራለች።

ሰኞ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዛ እንዳሉት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እቅድ ለማውጣቷ ምንም አይነት ማረጋገጫ እንደሌለ እና በድንበሩ ላይ ያለው የሰራዊት ግንባታዋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተረጋገጠ አይደለም ብለዋል።

ሩሲያ አብዛኛውን ጊዜ ጦሯን በፈለገችው ግዛቷ እንደምታሰማራ እና ይህ የዋሽንግተን ጉዳይ እንዳልሆነም አምባሳደር ቫሲሊ ተናግረዋል።

ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ክፍት ስብሰባ እንዳይደረግ ብትከላከልም 10 ለሁለት በሆነ ድምፅ ተሸንፋ ጉባዔው ተደርጓል።

የባይደን አስተዳደር “ውጥረቶችን በማነሳሳትና ትርክቶችን በመፍጠር ግጭቶች እንዲቀሰቀስ እየሰሩ ነው” ሲሉ አምባሳደሩ ወቅሰዋቸዋል።

"ይህ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ተቀባይነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለአካባቢው ትክክለኛ ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ እንዲኖረው እና በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ውጥረት ምክንያቶች መነሻ ነው በሚል ለማሳየት የሚደረግ ሙከራ ነው" ብለዋል።

አምባሳደር ቶማስ ግሪንፊልድ በበኩላቸው አሜሪካ አሁንም ቢሆን ለዩክሬን ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዳለ እንደምታምን ቢያስረዱም፤ ነገር ግን ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች አገራቸው ቆራጥ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች። የዚህ ውጤትም “አሰቃቂ” ነው ብለዋል።

"ይህ በአውሮፓ በአስርት አመታት ውስጥ ያላየነው ትልቁ የወታደር ማስፈር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ይህንን እየተናገርን ባለንበት ወቅት ሩሲያ ተጨማሪ ኃይሎችን እና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ድንበር እየላከች ነው” ብለዋል።

ሞስኮ በአጎራባቿ ቤላሩስና በዩክሬን ሰሜናዊ ድንበር ላይ የምታሰማራውን ጦር ወደ 30 ሺህ ለማሳደግ አቅዳ ነበር ሲሉ አስረድተዋል።

ሰኞ ምሽት ላይ የአሜሪካ መንግሥት ሰራተኞች ቤተሰብ አባላት ከቤላሩስ እንዲወጡ አሜሪካ አዛለች። ለዚህም “ያልተለመደው የሩሲያ ጦር ማስፈርን” ጠቅሳለች። ባለፈው ወር አሜሪካ በዩክሬን መዲና ኪየቭ የሚገኘውን ኤምባሲ ሰራተኞችና ቤተሰቦች እንዲወጡ አዛለች።