አሜሪካ የአዲስ አበባ አምባሳደሯን የሚተኩ ጉዳይ አስፈጻሚ መሾሟን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Tracey Jacobson/fb
አሜሪካ አዲስ አበባ ላለው ኤምባሲዋ ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ መሰየሟን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
አምባሳደር ጊታ ፓሲን በጊዜያዊነት በመተካት በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸው የተገለጸው ዲፕሎማት ትሬሲ አን ጃኮንሰን ናቸው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሹመቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ አዲሷ ጉዳይ አስፈጻሚ የሚተኩት በሥራ ላይ ያሉት አምባሳደር ጊታ ፓሲ ጡረታ ወጥተው በሌላ ሥራ ላይ መሰማራት በመፈለጋቸው መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ በፊት ኮሶቮን፣ ታጂክስታንን እና ቱርክሜንስታንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩት ጃኮብሰን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ይመራሉ ሲል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮንሰንን ለዚህ ኃላፊነት ሲመርጡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ እርዳታ ያለገደብ እንዲቀርብ ግጭቱን የሚያስቆም ድርድር እንዲደረግ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ሲያከናውኑ የነበረውን ተግባር ይቀጥሉበታል ተብሏል።
በአዲሷ ጉዳይ አስፈጻሚ የሚተኩት በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ ያገለገሉት ጊታ ፓሲ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ሆነው ሰርተዋል።
በተጨማሪም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከመስራታቸው ቀደም ብሎ ጊታ ፓሲ በጎረቤት አገር ጂቡቲ እና ቻድ ውስጥ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ የቅርብ አጋር ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ግንኙነታቸው ለአንድ ዓመት ያህል ሻክሮ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ወገን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው።
አሜሪካ በአዲስ አበባ ካላት አምባሳደር በተጨማሪ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው በመሰየም ወደ አካባቢው አገራት ሲመላለሱ ቆይተዋል።
አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ መተካታቸው ይታወሳል።












