የሰውን ልብ በንቅለ ተከላ ሕክምና በአሳማ ከመተካት ጋር በተያያዘ የሃይማኖት፣ የህክምናና የመብት ጥያቄዎች

የአሳማ ልብ ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና

የፎቶው ባለመብት, UMSOM

ታትሟል

አሜሪካዊው ግለሰብ በዘረ መል ምህንድስና (ጄኔቲክ ኢንጂኔሪንግ) የተሻሻለ የአሳማ ልብ በንቅለ ተከላ በማግኘት ከዓለም የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

ክፉኛ ታሞ ነበረው የ57 ዓመቱ ዴቪድ ቤኔት ለሰባት ሰዓታት ከተደረገለት የሙከራ ቀዶ ሕክምና በኋላ ባሳለፋቸው ቀናት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ዶክተሮች ገልጸዋል።

ቀዶ ህክምናው ረዥም ጊዜ ይወስድ የነበረውን የሕክምና ጊዜን የሚያሳጥር እና በዓለም ላይ ያሉ የልብ ህሙማንን ህይወት ሊለውጥ የሚችል የሕክምና ግኝት ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እየተወደሰ ነው።

አንዳንዶች ግን ከሥነ ምግባር አኳያ ተገቢ ስለመሆኑ ይጠይቃሉ።

በታካሚዎች ደኅንነት፣ በእንስሳት መብት እና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሞራል ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉም እየተነገሩ ነው።

የአሳማ ልብ የንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምና ምን ያህል አከራካሪ ነው?

የሕክምናው አንድምታ

ይህ የሙከራ ቀዶ ሕክምና ሲሆን በታካሚውም ላይ ትልቅ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በደንብ ሊጣጣሙ ይችላሉ ተብለው ከሰዎች ለታካሚዎች የሚሰጡ አካላት ጭምር ከሕክምና በኋላ ላይሳኩ ይችላሉ።

ጭራሽ የእንስሳት አካል ሲሆን ደግሞ አደጋው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

ዶክተሮች ለብዙ አሥርተ ዓመታት 'ዜኖትራንስፕላንቴሽን' በመባል የሚታወቀውንና የእንስሳት አካላትን በንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምና ለመጠቀም ሲሞክሩ ቆይተዋል። በእነዚህ ንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምናዎች ያለው ውጤት ግን ወጥ አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1984 የካሊፎርኒያ የሕክምና ባለሙያዎች አንዲትን ህጻንን ለማዳን የዝንጀሮ ልብ በንቅለ ተከላ ቢተኩላትም ከ21 ቀናት በኋላ ህይወቷ አልፏል።

እንደእነዚህ ያሉት ሕክምናዎች እጅግ በጣም አደገኛ ቢሆኑም አንዳንድ የሕክምና የሥነ-ምግባር ባለሙያዎች በሽተኛው ጉዳቱን እስካወቀ ድረስ ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት ይናገራሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኡሂሮ የሥነ ምግባር ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ጁሊያን ሳቩለስኩ "ከንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምናው በኋላ ግለሰቡ እንደሚሞት በፍጹም ማወቅ አይቻልም። ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች አደጋውን ከግምት ውስጥ አስገብተው ነው ሥራቸውን የሚያከናውኑት" ብለዋል።

አክለውም "ታካሚዎች የአደጋዎቹን መጠን እስከተረዱ ድረስ ሰዎች በእነዚህ ስር ነቀል በሆኑ ሙከራዎች መስማማት መቻል አለባቸው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

ፕሮፌሰር ሳቩለስኩ እንደሚሉት ታካሚዎች ሰው ሰራሽ ልብን ጨምሮ የሰው ልብን በንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምና መተካትና ሌሎች አማራጮች ሊቀርብላቸው እንደሚገባ አፅንኦት ይሰጣሉ።

የቤኔትን ሕክምና ያከናወኑት ዶክተሮች ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ እና ይህ ሕክምና ካልተደረገለት ስለሚሞት ቀዶ ህክምናው ትክክለኛ ነው ብለዋል።

የአሳማ ልብ ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና የተደረገለት ዴቪድ ቤኔት

የፎቶው ባለመብት, University of Maryland School of Medicine

የምስሉ መግለጫ, የአሳማ ልብ ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና የተደረገለት ዴቪድ ቤኔት

ሆኖም ፕሮፌሰሩ እንደሚያስረዱት ቀዶ ሕክምናው ከመደረጉ በፊት አሠራሩ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ "በህዋሶች ላይና በእንስሳት ላይ የሙከራ ሂደቶች ማለፍ አለበት" ይላሉ።

የቤኔት ንቅለ ተከላ የሙከራ ቀዶ ሕክምና ቢሆንም በሰዎች ላይ በሰፊው በተግባር ከመዋሉ በፊት እንደሚሆነው በክሊኒካዊ ሙከራ መልኩ አልተካሄደም። የተሰጡት መድኃኒቶችም የሳይንስ ሕጉ በሚያዘው መሰረት በእንስሶች ላይ ሙከራ አልተደረገባቸውም።

ነገር ግን የቤኔትን ሕክምና በማቀድ የተሳተፉት የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ክርስቲን ላው ለሕክምናው ሁሉንም ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውንና ምንም አይነት ስጋቶች ችላ አለመባላቸውን አስታውቀዋል።

"ንቅለ ተከላው ለሰው ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲውል ለማስቻል ለአስር ዓመታት ያህል በቤተ ሙከራ ውስጥ በእንስሳት ላይ ሞክረናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእንስሳት መብቶች ጥያቄ

የቤኔት ሕክምና ብዙ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች የሚቃወሙትን የአሳማን አካል ለሰው ልጅ በንቅለ ተከላ መጠቀምን የክርክር ርዕስ እንደገና ቀስቅሶታል።

ከእነዚህም መካከል ሰዎች ለእንስሳት ሥነ ምግባራዊ ሕክምና (ፒኢቲኤ) የተባለው ተቋም የቤኔትን የአሳማ ልብ የማግኘት ቀዶ ሕክምና "ሥነ ምግባር የጎደለው፣ አደገኛ እና ከፍተኛ የሃብት ብክነት" በማለት አውግዞታል።

"እንስሳት ዝም ብለው በዘፈቀደ የሚታረዱ መጠቀሚያ አይደሉም። ውስብስብ እና አስተዋይ ፍጡራን ናቸው" ሲል ፒኢቲኤ ገልጿል።

ተቃዋሚዎቹ የእንስሳትን ዘረ መል የሰው እንዲመስሉ ማሻሻል ስህተት ነው ይላሉ። ሳይንቲስቶቹ የቤኔት ሰውነት እንዲቀበለው በሚል ለቤኔት ንቅለ ተከላ የተጠቀሙበትን የአሳማ ልብ 10 ዘረ መሎች ላይ ማሻሻያ አድርገዋል።

የአሳማው ልብ በቀዶ ህክምናው ዕለት ጠዋት ነበር የወጣው።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የእንስሳት እርዳታ ድርጅት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእንስሳትን ዘረ መል ማሻሻል ወይም የእንስሳትን አካል በንቅለ ተከላ (ዜኖትራንስፕላንት) መጠቀም "በማንኛውም ሁኔታ" እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።

"እንስሳ ህመም እና ስቃይ የሚያመጣባቸውን የዘረ መል ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ህይወታቸውን የመምራት መብት አላቸው። መጨረሻም ላይ ይህንን አልፈው መታረድ እና አካላቸውን መቀራመት ተገቢ አይደለም" ሲል ድርጅቱ ተቃውሟል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የዘረ መል ማሻሻያው በአሳማው ጤና ላይ የማይታወቁ የረዥም ጊዜ ተጽዕኖዎች ሊኖሩት ይችላል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የባዮኤቲክስ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ዴቮልደር "በእንስሳት ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ እርግጠኛ መሆን እስከከቻልን ድረስ" ዘረ መላቸው የተሻሉ የአሳማዎችን የአካል ክፍሎች በንቅለ ተከላ መጠቀም ያለብን ይላሉ።

"አሳማዎችን ለሥጋቸው መጠቀም ህይወትን ለማዳን ከማዋል የበለጠ ችግር አለው። በዚህም ቢሆን የእንስሳትን ደኅንነት ችላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለውም" ይላሉ።

አሳማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሃይማኖት ጥያቄ

አሳማዎች ለንቅለ ተከላ ቀዶ ሕክምና የሚመረጡት አንዳንድ አካላቸው ከሰዎች ጋር ተመሳሳይነት ስላቸውና በተጨማሪም አሳማዎች በአንጻራዊነት ለመራባት እና ለማደግ ቀላል ስለሆኑ ነው።

ነገር ግን ይህ ሁኔታ አሳማ ላይ ጥብቅ የክልከላ ደንብ ያላቸው ሙስሊምና የአይሁድ ታካሚዎች ጋር እንዴት ሊጣጣም ይችላል?

በአይሁድ ሕግ መሰረት አሳማን ማሳደግም ሆነ መብላት ይከለክላል፣ ሆኖም የአሳማ ልብ መቀበል "በምንም መልኩ የአይሁድን የአመጋገብ ሕግጋት መጣስ አይደለም" ይላሉ በእንግሊዝ የጤና ሚኒስቴር የሞራል እና ሥነ ምግባር አማካሪ ቡድን (ኤምኢኤጂ) አባል የሆኑት ከፍተኛው የለንደን ራባይ ዶክተር ሞሼ ፍሪድማን።

ፍሪድማን "በአይሁዶች ሕግ መሠረታዊው ጉዳይ የሰውን ህይወት መጠበቅ መሰረታዊ በመሆኑ የአሳማ ንቅለ ቀዶ ሕክምናን ማካሄድ ከፍ ያለ የመትረፍ ዕድል እና የተሻለ ህይወት የሚሰጥ ከሆነ አንድ አይሁዳዊ የእንስሳትን አካል በንቅለ ተከላ የመቀበል ግዴታ አለበት" ብለዋል ለቢቢሲ።

በእስልምናም በኩል የእንስሳትን አካልን መጠቀም የሰውን ህይወት ከታደገ የሚፈቀድበት ተመሳሳይ ሁኔታ አለ።

የግብፅን ሃይማኖታዊ ውሳኔዎች እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ዳር አል-ኢፍታ የተሰኘው ተቋም "የታካሚው ህይወት ስጋት ላይ የሚወድቅ ከሆነ፣ የአካል ክፍሎች መቆረጥ ወይም መታመም፣ የበሽታ መባባስ ከተፈጠረ የአሳማ ልብ ይፈቀዳል" ይላል።

ፕሮፌሰር ሳቩለስኩ እንደሚሉት አንድ ሰው በሃይማኖታዊ ወይም በሥነ ምግባር ምክንያቶች የእንስሳት አካል ንቅለ ተከላውን ባይቀበል በሰው አካል ለጋሾች መጠባበቂያ ዝርዝር ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"አንዳንድ ሰዎች አንድ ጊዜ አካሎችን ለመለገስ እድል ካገኙና ካልተጠቀመበት ከዝርዝሩ ስማቸው ሊወርድ ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ እንደማንኛውም ሰው መብት ሊኖራቸው ይገባል ይሉ ይሆናል" ይላሉ።

"እነዚህን አቋሞች እያየን እያስታረቅን መሄድ ነው ያለብን" ብለዋል።