በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ በሕዝብ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሞቱ

የአልሻባብ ታጠቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ, ለአሁኑ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ወገን ባይኖርም የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ከዚህ በፊት በማንዴራ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽሟል
ታትሟል

ኬንያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት በሰሜን ምሥራቅ የድንበር ከተማዋ ማንዴራ ውስጥ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሞቱ።

በአካባቢው ያሉ ጋዜጠኞች እንደሚሉት በቦምብ ፍንዳታው ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው በተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት ወደ ሚያጋጥማት በድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ማንዴራ ከተማ እያመራ ነበረ።

በአካባቢው ካሉ ጋዜጠኞች በኩል የወጡ ፎቶግራፎች እንደሚያሳዩት የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመበት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አካል ክፉኛ ተጎድቷል።

ኬንያ ውስጥ ማታቱ በመባል የሚታወቁት የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ መኪና መንገዱ ላይ በተጠመደ ቦምብ ጉዳት እንደደረሰበት ተነግሯል።

አስካሁን ድረስ ለዚህ አደጋ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የሌለ ሲሆን፣ ነገር ግን የሶላማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ፖሊሶችንና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በአካባቢው በመፈጸም፣ ማንዴራን ኬንያ ውስጥ ለኑሮ በጣም አደገኛ የሆነች ስፍራ አድርጓታል።

ይህ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ያጋጠመው አሜሪካና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ በኬንያ የሚገኙ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች በአገሪቱ ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ካስጠነቀቁ ከቀናት በኋላ ነው።

ይህንን ማስጠንቀቂያ ተከትሎም የኬንያ ፖሊስ አስፈላጊውን የደኅንነት ጥበቃ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ባወጣው መግለጫ የሕዝቡ ደኅንነት የተጠበቀ መሆኑን አመልክቷል።

በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውና ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው እስላማዊው ቡድን አልሻባብ ከዚህ ቀደም ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተደጋጋሚ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን መፈጸሙ ይታወቃል።