የቤጂንግ ኦሊምፒክ፡ በጥብቅ ቁጥጥር ሥር እና በዲፕሎማሲያዊ ዕቀባ ውስጥ የሚከወነው 'ቀዝቃዛው' የክረምት ኦሊምፒክ

ዪይ ከእናቷ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ዪይ እና እናቷ ወደ የትኛውም የውድድር ሥፍራ መሄድ አይችሉም
ታትሟል

ዛሬ የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክ ይጀመራል። በኦሊምፒክ ታሪክ እንዲህ አይነት 'ቀዝቀዝ' ያለ ውድድር ታይቶ የሚታወቅ አይመስልም።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ በተቃራኒም ውድድሩ አንድ ከተማ ተጀምሮ በዚያው ከተማ ይጠናቀቃል።

ቤጂንግ ሁሉንም ውድድሮች የምታስተናግድ ብቸኛዋ ከተማ ናት። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክፉኛ ያጠላበት ይህ ውድድር የሚከናወነውም በጥብቅ መመሪያዎች ውስጥ ነው።

ቻይና ከሰብአዊ መብት ረገጣ ጋር በተያያዘ እየቀረበባት ባለው ውንጀላ አሜሪካና ዩኬን ጨምሮ በርካታ የምዕራባውያን አገራት ለውድድሩ የዲፕሎማቲክ ልዑክ ላለመላክ ራሳቸውን አቅበዋል። ይህ ቻይናን ክፍኛ ያበሳጨ ድርጊት ነበር። ውድድሩንም አላቀዘቀዘውም ማለት አይቻልም።

የኦሊምፒክ ውድድር ለማከናወን የተዘጋጁት አብዛኞቹ የበረዶ ሥፍራዎች ሰው ሰራሽ ናቸው።

ይህ ሁሉ ግን የበረዶ መንሸራተቻ ላይ ልምምድ እያደረገች ላለችው የ6 ዓመቷ ታዳጊ ዪይ ግድ አይሰጥም። ውድድሩ እስኪጀመር በጉጉት ልምምዷን ብቻ ታዳርጋለች።

ዪይ ቤጂንግ ኦሊምፒክን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታስተናግድ አልተወለደችም ነበር።

ከአሰልጣኝ ጋር ልምምድ እያደረገች ያለችውን ልጇን እየተመለከተች ያላቸውን እናት የቢቢሲ ዘጋቢ ቀረብ ብሎ ሲያናግራት "ልምምዷ በጣም አድካሚ ነው፤ ነገር ግን ታልፈዋለች" ብለዋለች።

"ሁሉንም እንቅስቃሴዎች እንዴት ማድረግ እንዳለባት እስክትማር ድረስ የትም አትሄድም። አታቋርጥም" ስትልም አክላለች።

ሆኖም ዪይ እና እናቷ ወደ የትኛውም የውድድር ሥፍራ መሄድ አይችሉም። የክረምት ኦሊምፒክ በቤጂንግ እየተካሄደ ነው፤ ነገር ግን ውድድሩን መታደም አይችሉም።

ቻይና "ዜሮ ኮቪድ" በሚል መርህ አንድም ሰው በኮሮና እንዳይያዝ የሚጥር የጤና መርሃ ግብር ላይ ነች።

በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ወደ ውድድር ሥፍራዎች ለመግባት የሚያስችል ምንም ዓይነት ትኬቶች ለሕዝብ እንዳይሸጥና ሕዝብ ውድድሩን እንዳይታደም ወስነዋል።

ውድድሩን ቦታው ድረስ በመሄድ መመልከት የሚችሉት የገዥው ኮሚኒስት ፓርቲ አባላት ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ኩባንያዎች ሰራተኞች ብቻ ናቸው። እነሱም ቢሆኑ ወደ ውድድር ሥፍራው ሲገቡ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረግ እና ጥብቅ ገደቦችን ማክበር ግድ ይላቸዋል።

የዪይ እናት ውድድሩን በቲቪ ከመከታተል ውጪ አማራጭ እንደሌላት ስታውቅ ለቢቢሲ ዘጋቢ ምን ያህል እንዳዘነች ገልጻለች።

ታዳሚዎች የቻይና ጥብቅ የኮቪድ መከላከያ መመሪያ የሚተገበርባቸው አንድ አካል ይሁኑ እንጂ ይህ ለተወዳዳሪዎችም የሚቀር አይደለም።

ስፖርተኞች እና አመራሮቻቸው ማንኛውንም የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በተዘረጉ ጥብቅ መመሪያዎች ውስጥ ናቸው። ከገቡም መውጣት አይችሉም። በውድድሩ ከሕዝብ ጋር የሚገናኛቸውን ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግም ቀዩ መስመር ነው። ድንገት ወጣ ካሉ እንኳን ከተሽከርካሪያቸው መውጣት አይፈቀድላቸውም።

እዚህ ውድድር ላይ ጥላ ያጠላው ይህ ጥብቅ የኮቪድ መመሪያ ብቻ አይደለም።

በቻይና የሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ መካረር አለ። ይህንን ሰበብ አድርገው አሜሪካ፣ ዩኬ እና ሌሎች በርካታ አገራት ውድድሩን ለመታደም የመንግሥታቸውን ከፍተኛ ባለሥልጣናት አልላኩም።

የቻይና መሪዎች እና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዲፕሎማሲያዊ ዕቀባቸውን "ፖለቲካዊ" እያሉ ሲያጣጥሉት መስማት የተለመደ ነው።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከዪይ ጋር በተገናኙበት የበረዶ መለማመጃ ላይ ልጁን ሲያጫውት የነበረን አንድ አባት ስለዚህ ጉዳይ ጠይቆት "ውድድሩ ስፖርት ብቻ ነው" የሚል ምላሽን ሰጥቷል። ፖለቲካን እዚህ ጋር ምን አመጣው ነው ነገሩ።

"እኔ እንደማስበው ስፖርት ስፖርት ነውና ከፖለቲካ ጋር መቀላቀል የለበትም። ውድድሮቹ የሁሉም ናቸው። ስለዚህ በጋራ መታደም አለብን። ፖለቲካ ፖለቲካ ነው" ሲል ተናግሯል።

በግርድፍ ትርጉሙ 'ለመጪው የጋራ ጊዜ በጋራ መሆን' የሚለው የዘንድሮ የቤጂንግ ይፋዊ መሪ ሃሳብ አለው። ይህ መሪ ሃሳብ ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አንደበት ከማይጠፉት ንግግሮች ጋር ተመሳሳይ ነው። ፕሬዚደንቱ ለሰው ልጅ የወደፊት የጋራ ሕይወት መገንባት የሚል አይነት ትልም አላቸው።

ይህ አባባል ቤጂንግ ውስጥ የትም ይታያል። በአውቶብስ ፌርማታዎች፣ በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ እና በቤጂንግ ባለ ለማስታወቂያ በሚሆን በየትኛውም ግድግዳ ላይ ይህ ጹሁፍ አለ። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚያሰራጩት ቪዲዮዎች ውስጥም ይህ ሃሳብ አለ። በኢንተርኔት ይህንን ሃሳብ የሚንጸባሩቁ ቪዲዮችም እንደልብ ናቸው።

ልጆች ይፋዊውን የቤጂንግ 2022 መፈክር ይዘው ሲደንሱ እና ሲዘፍኑ

የፎቶው ባለመብት, XINJIANG REGIONAL MEDIA

የምስሉ መግለጫ, ልጆች ይፋዊውን የቤጂንግ 2022 መፈክር ይዘው ሲደንሱ እና ሲዘፍኑ

ይህ መሪ ሃሳብ ይፋ የተደረገው ባለፈው ወር ሲሆን ቻይና ኡይጉር በተባሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰብ አባላት ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች መባሉን ካስተባበለች በኋላ ነው።

በዚህ ጉዳይ ቢቢሲ ያነጋገረው እና ከአሜሪካ አትሌቶች ጋር ቅርበት ያለው ኖህ ሆፍማን የተባለ የቀድሞ ኦሊምፒክ ተሳታፊ ሰዎች ስለዚህ አባባል ለምን ይጨናቃሉ ሲል ይጠይቃል።

"አንድም ስፖርተኛ በጨዋታው ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚናገር አይመስለኝም። ይህ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። "እዚያ ብሆን ኖሮ ዝም ማለቴ አይቀርም ነበር" ብሏል።

ይህንን ሃሳብ ለቢቢሲ ያጋራው የ32 ዓመቱ የበረዶ መንሸራተት ተወዳዳሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 እና 2018 አሜሪካን ወክሎ ተወዳድሯል። አሁን ከውድድር ውጪ ቢሆንም ለስፓርተኞች መብት ይሟገታል።

"አደጋው በጣም ትልቅ ነው... ይህ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ድክመት ነው። አትሌቶች በዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ መሆናቸው የአመራር ድክመት ነው" ሲል ተናግሯል።

በቤጂንጉ ውድድር ተሳታፊ ከሆኑት የቡድኑ አጋሮች ጋር እንደሆነ የተነገረው የቀድሞ የኦሊምፒክ ተሳታፊ " ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ነገር ገጥሟቸው እንደማያውቅ" እንደነገሩት ገልጿል።

አንድ አትሌት ስለ "ስፖርት ወይም የአትሌቲክስ ብቃታቸው" አንድም ስብሰባ እንዳልተደረገ ነግረውኛል ብሏል። ከአሜሪካ የኦሊምፒክ ቡድን አመራሮች ጋር የተካሄደው ስብሰባ በኮቪድ-19 መመሪያዎች እና በቻይና በሚቆዩበት ወቅት ተወዳዳሪዎች ሊያደርጉት ስለሚገባ ጥንቃቄ ብቻ ገለጻ እንደተደረገላቸው አክሏል።

በውድድሩ አትሌቶች ያላቸውን ቅሬታ እንዲገልጹ የሚፈቅድላቸው የተሻሻሉ ሕጎች የወጡ ቢሆንም የቻይና ባለሥልጣናት አትሌቶች በማንኛውም ጊዜ የቻይናን ሕግ ማክበር እንዳለባቸውም አስጠንቅቀዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ውጤታማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ውድድር እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል። በብዙ መልኩ ይህ ውድድር የተለመደው አይነት ኦሊምፒክ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።

የኦሎምፒክ ችቦው ተልኩሷል። በከተማ ውስጥ የኦሎምፒክ ምልክቶች በብዛት ይታያሉ። የኦሎምፒክ መለያዎች በገበያና አገልግሎት መስጫዎች ላይም ይስተዋላሉ።

ሆኖም ውድድሩ የቻይና እና የአሜሪካ ፍጭት፣ ጥብቅ የኮቪድ መመሪያዎች እና የተለያዩ መንግሥታት የዲፕሎማሲ ልዑክ ዕቀባ ጥላ ያጠላበት ይመስላል።

የሆነው ሆኖ ግን ተወዳዳሪዎች ውጤት ለማስመዝገብ መትጋታቸውን ቀጥለዋል።