የኤርትራ ብስክሌተኞች በኮቪድ ክትባት ምክንያት በሩዋንዳ በሚደረገው ውድድር አይሳተፉም

የፎቶው ባለመብት, Mekseb
የኤርትራ ብሔራዊ የብስክሌት ውድድር ቡድን ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር 'ቱር ዴ ሩዋንዳ' እንደማይሳተፉ ተገለጸ።
ለዚህም ምክንያቱ የቡድኑ አባላት የኮሮናቫይረስ መከለካከያ ክትባት ባለመከተባቸው የውድድሩን መስፈርት ስለማያሟሉ ነው።
የውድድሩ አዘጋጆች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክትባቱን የወሰዱ ተወዳዳሪዎች ብቻ ይሳተፋሉ።
ኤርትራ ለዜጎቿ የኮሮናቫይረስ ክትባት መስጠት ያልጀመረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ነች።
በሌላ በኩል ሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ጠንካራ ቁጥጥር የምታካሂድ አገር ስትሆን፤ በተደጋጋሚ ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ በማድረግ ጭምር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
በተገባደደው ሳምንት የሩዋንዳ መንግሥት ዜጎች ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ለመገኘት ክትባት መውሰድ እንደሚገባቸው አሳስቧል።
በአፍሪካ ስኬታማ የብስክሌት ተወዳዳሪ ቡድን ተብሎ የሚታወቀው የኤርትራ ቡድን፣ በቱር ዴ ሩዋንዳ ላይ እንደማይሳተፍ የተገለጸው አዘጋጆቹ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ነው።
ቱር ዴ ሩዋንዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ታዋቂነቱ እየጨመረ የመጣ ውድድር ነው። እአአ በ2019 በዓለም አቀፉ የሳይክል ማኅበር እውቅና አግኝቷል።
ከእውቅናው በኋላም ከመላው ዓለም የተለያዩ ተወዳዳሪዎችን የሳበ ሲሆን ኤርትራዊያኑ ናትናኤል ተስፋጽዮን እና መርኃዊ ቅዱስ አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል።












