ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣሊያን ተተኪ መሪ ላይ ከስምምነት ባለመድረሷ የ80 አመቱ ፕሬዚዳንት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ተወሰነ
በጣሊያን ጥምር ፓርቲዎች የአገሪቱን ተተኪ መሪ ለመምረጥ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላቸውን ተከትሎ የ80 አመቱ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ለሁለተኛ ጊዜ ለማገልገል ተስማምተዋል።
በሮም ውስጥ ለስድስት ቀናት ያህል የተካሄደውን ውጥረት የተሞላበት ምርጫ ተከትሎ የ80 አመቱ አዛውንት በሁሉም ዘንድ ተመራጭ ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ ለጣልያን "መረጋጋት" ሲሉ ከኃላፊነታቸው እንዳይወርዱ እንዳሳመኗቸው ዘግበዋል።
ስምንተኛ ዙር ምርጫን ተከትሎ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ እለት በይፋ በድጋሚ ተመርጠዋል።
ቅዳሜ እለት መመረጣቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ባደረጉት ንግግር ሃገሪቱ ካጋጠሟት የጤና እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች አንፃር በስልጣን ላይ ለመቆየት "የኃላፊነት ስሜት" እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
የቀድሞው የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኛና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አክለውም "ከግል ምርጫዬ በላይ የአገር ግዴታ የበላይ መሆን አለበት" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ ፕሬዚዳንቱ በድጋሚ መመረጣቸው "ለጣሊያኖች አስደሳች ዜና" ሲሉ አወድሰውታል።
አክለውም " ፓርላማው ፕሬዚዳንቱን ለሁለተኛ ጊዜ ለመምረጥ ያለውን እጅግ ጠንካራ ፍላጎት ለመቀበል ያደረጉትን ውሳኔ አመሰግናለሁ" ብለዋል።
የጣሊያን የአስተዳደር ጥምረት ፓርቲዎች ተተኪ እጩ ለማቅረብ ሰባት ዙር ምርጫ ቢያደርጉም በካቢኔ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል ካጋጠማቸው በኋላ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላን በድጋሚ ለመምረጥ ተስማምተዋል።
የጣሊያን ፕሬዚዳንት የሚመረጠው 1,009 ሴናተሮች፣ የፓርላማ አባላት እና አንዳንድ የክልል ተወካዮች ባሉበት የኤሌክቶራል ኮሌጅ በሚስጥር ድምፅ ሲሆን፣ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ያገኘውም አሸናፊ ይሆናል።
ነገር ግን በአሁኑ ምርጫ እጩ ተብሎ የቀረበው ግለሰብ ያገኘው ድምፅ 759 ብቻ ነው።
በርካታ የህግ አውጭዎች በድምጸ ተዓቅቦ አንመርጥም በማለታቸውና የገዥው ፓርቲው ያቀረቧቸው እጩዎች በቂ ድጋፍ ማሰባሰብ ባለመቻላቸውም ነው ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ የበርካቶች የፓርላማ አባላት ምርጫ የሆኑት።