ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመድ ባለሙያዎች ገዳዮች ላይ የሞት ቅጣት ፈረደች
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎችን በመግደል እጃቸው አለበት የተባሉ በርካታ የሚሊሺያ አባላት በሞት እንዲቀጡ ተበይኖባቸዋል።
የስዊድንና ቺሊ ጥምር ዜግነት ያላቸው ዛይዳ ካታላን እና አሜሪካዊው ሚካኤል ሻርፕ በካሳይ ግዛት ታፍነው የተወሰዱትና የተገደሉት በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር።
የተመድ ሰራተኞቹ በመንግሥት ኃይሎች እና በሚሊሺያ ቡድኖች መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ተገኙ የተባሉ የጅምላ መቃብሮችን በማጣራት ላይ ነበሩ።
የባለሙያዎቹም አስተርጓሚ ቤቱ ትሼንትላም ተገድለው ተገኝተዋል። ግለሰቦቹ ታፍነው ከተወሰዱ ከ16 ቀናት በኋላም አስከሬናቸው ተገኝቷል።
ዛይዳ ካታላን የተገደሉት አንገታቸው ተቀልቶ ነበር።
በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በግድያው መደናገጡን ያሳወቀ ሲሆን የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ተመድ "ፍትህ እንዲገኝ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል" ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2017 የተቋጨው የካሳይ ግዛት ግጭት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
የአካባቢው መሪ ካምፒውና ሳፑ በአውሮፓውያኑ 2016 መገዳላቸውን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት ከሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የፍርድ ሂደቱ አራት አመት የፈጀ ሲሆን የጥፋተኝነት ብይን የተላለፈው በአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ነው።
በሰራተኞቹ ግድያ ከቀረቡት አምሳ አንዱ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የሚሊሺያ አባላት ሲሆኑ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፤ ነገር ግን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሞት ቅጣትን የሻረች ሲሆን የግለሰቦቹም ቅጣት ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊቀየር እንደሚችል ተጠቁሟል።
ግለሰቦቹ በሽብርተኝነት፣ በነፍስ ግድያና ሆን ብሎ አካላትን በማጉደል የጦር ወንጀሎችን እስከመፈጸም ድረስ የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸዋል ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኮሎኔል ዣን ደ ዲዩ ማምብዌኒ በበኩላቸው ትዕዛዝ በመጣስ የአስር አመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ሁለት ግለሰቦች፣ ጋዜጠኛ እና የፖሊስ መኮንን በነፃ ተለቀዋል።