በአሜሪካ የኮቪድ ክትባት ያልተከተበው ግለሰብ የልብ ንቅለ ተከላ ተሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, CBS
በአሜሪካ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ታካሚው የኮቪድ-19 ክትባት ባለመውሰዱ የልብ ንቅለ ተከላውን ሰረዘ።
ዲጄ ፈርጉሰን የተሰኘው የ31 ዓመት ታካሚ አንገብጋቢ የሆነ የልብ ንቅለ ተከላ የሚያስፈልገው ቢሆንም በቦስተን የሚገኘው ሆስፒታል ግን ግለሰቡን ከታካሚዎች ዝርዝር ውስጥ አስወጥቶታል።
የብሪንግሃም እና የሴቶች ሆስፒታል የልብ ንቅለ ተከላውን የሰረዘው ታካሚው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ባለመውሰዱ ነው።
የታካሚው ወላጅ አባት ዴቪክ፤ የኮቪድ ክትባት ከልጃቸው መሠረታዊ መርሆች ጋር የሚቃረን መሆኑን በመግለጽ ልጃቸው በክትባት እንደማያምን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በበኩሉ ንቅለ ተከላውን የሰረዝኩት መመሪያ በመከተል ነው ብሏል።
"በውስጥ አካላት ጉዳት ምክንያት በንቅለ ተከላ አዲስ የውስጥ አካል የተቀበለ ታካሚ በሕይወት የመትረፍ እድሉ ከፍተኛ እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲል የብሪግሃም እና የሴቶች ሆስፒታል ለቢቢሲ ገልጿል።
የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ሆስፒታላቸው የታካሚዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ከግምት በማስገባት ንቅለ ተከላው የመሳካት እድሉን እና ታካሚዎች ከቀዶ ጥገናው በኋላ የመትረፍ እድላቸው ከፍ ለማድረግ ከንቅለ ተከላ በፊት የኮቪድ-19 ክትባት እና የአኗኗር ዘይቤዎችን እንደሚመለከቱ ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ የአካል ክፍሎችን ለመተካት በተጠባባቂ መዝገብ ውስጥ ከሚገኙት 100,000 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአምስት ዓአመት ጊዜ ውስጥ የውስጥ አካል እንደማያገኙ እና የአካል ክፍሎች እጥረት ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፈርጉሰን ባጋጠመው የልብ ሕመም ምክንያት ላለፉት አራት ወራት ሆስፒታል ተኝቶ በመታከም ላይ ይገኛል።
ለግለሰቡ ገንዘብ ለማሰባሰብ በተዘጋጀው የጎ ፈንድ ሚ አካውንት ላይ አዘጋጆቹ እንደገለጹት ፈርጉሰን ክትባቱን ከወሰደ በልቡ ላይ ተጨማሪ ሕመሞች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሰግተዋል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ኤጄንሲ ሲዲሲ በበኩሉ የንቅለ ተከላ ተቀባዮች እና በአቅራቢያቸው ያሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንዲከተቡ እንዲሁም ተጨማሪ የማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱ ያበረታታል።
ዶ/ር አርተር ካፕላን በኒዩ ግሮስማን የሕክምና ትምህርት ቤት የሕክምና ሥነ ምግባር ኃላፊ ናቸው። ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ ማንኛውም የሰውነት አካል ከተቀየረ በኋላ የታካሚው በሽታ የመከላከል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይዘጋል። በተጨማሪም በተራ ጉንፋን እንኳን ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
"የውስጥ አካል ክፍሎቹ በጣም አነስተኛ ቁጥር ስላላቸው አናሳ የመዳን እድል ላለው ሰው ላለመስጠት እንሞክራለን። ሌሎች ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎች ከንቅለ ተከላው በኋላ የመዳን እድላቸው ከፍተኛ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ወላጅ አባቱም ልጃቸው በራሱ ሰውነት ላይ የመወሰን መብት እንዳለው እና ሕመሙንም በጀግንነት እየታገለ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ግዜ ውስጥ ባሳየው ቁርጠኝነትም ለልጃቸው ያላቸው ክብር መጨመሩን ተናግረዋል።












