ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ዶ/ር ቴድሮስን ዳግም ዕጩ አድርጎ አቀረበ
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ድርጅቱን ዳግም ለቀጣይ አምስት ዓመታት በዳይሬክተርነት እንዲመሩ ዕጩ አደረገ።
ድርጅቱን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ዶ/ር ቴድሮስ ያለተፎካካሪ ብቸኛ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን የመጨረሻው ውጤትም ግንቦት 2014 ዓ.ም. ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ኃላፊነታቸውን ከአምስት ዓመት በፊት ከመረከባቸው ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የጤና ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
ዶ/ር ቴድሮስ ከአምስት ዓመታት በፊት ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የኢትዮጵያ ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር። ይሁን እንጂ የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዶ/ር ቴድሮስ ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ለህወሓት ድጋፍ ያደርጋሉ ሲል በተደጋጋሚ ከሷቸዋል።
የዓለም ጤና ደርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በጄኔቭ ለስበሰባ ከመቀመጡ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በዶ/ር ቴድሮስ ገለልተኝነት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ በዳይሬክተሩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የቀረበውን የኢትዮጵያ ጥያቄ ወደ ጎን በመግፋት ሳይመለከተው ቀርቷል።
ዶ/ር ቴድሮስ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ዕጩ በሆኑበት ጉዳይ ላይ ለመወያየት በተጠራ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ፓትሪክ አሞት አቤቱታውን ያልተመለከቱበትን ምክንያት ገልጸዋል።
"ይህ ጉዳይ በጣም የተወሳሰበና ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው፤ ከዚህ ኮሚቴ የአስራር ማዕቀፍ ውጪ ነው" አሞት ያሉ ሲሆን፤ የቦርዱ 34 አባላት በሙሉ የምርመራ ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ በጉዳዩ ላይ በተወያየበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የአገራቸውን አቤቱታ ለማብራራት በመከሩበት ጊዜ እንዲያቋርጡ ተደርገው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ በድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ንግግር እንዳያደርጉ መከልከሉ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ውሳኔው የዓለም ጤና ድርጅት በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ አለመሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ የዓለም ጤና ድርጅት በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ይጠይቃልም ሲሉ ለሮይተርስ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የድርጅቱን ነፃነት፣ ገለልተኝነት መርህ ጥያቄ ውስጥ እንደከተቱት በመጠየቅ ምርመራ እንዲደረግ አቤቱታ አቅርቦ ነበር።
በትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓመታት አባልና አመራር የነበሩበትን ህወሓት የሚደግፉ ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ሲሉ ሲከሱ ቆይተዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ እና የዓለም ጤና ድርጅት
የቢቢሲ የጄኔቭ ዘጋቢ ኦሞጂን ፉክስ እንዳለችው የትኛውም የከዚህ ቀደም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር እንደ ዶ/ር ቴድሮስ አልተፈተነም።
የኮቪድ-19 ወረርሸኝ፣ ቻይና ስለ ወረርሽኑ መረጃ እንድታጋራ ጫና ማድረግ፣ ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተፈጠረው እሰጣገባ፣ የአሜሪካ ድጋፍ ማቆም እና ከድርጅቱ አባልነት መውጣት በቀዳሚነት የሚወጠቀሱ ሲሆን።
ለአንድ ዓመት የዘለቀው የትግራዩ ጦርነት በግል ያደረሰባቸው ጫና እና ከትውልድ አገራቸው መንግሥት ጋር የገቡት ቅሬታ የዶ/ር ቴድሮስ ፈተናዎች ከነበሩት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
አሁንም ቢሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዝርያውን እየቀረ ዓለም ማሸበሩን አላቆመም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሁንም የኮቪድ ክትባትን አልወሰዱም።
የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ፈጽመውታል በተባለው የጾታ ጥቃት የድርጅቱን የከበረ ስም አጉዱፏል።
በሌላ በኩል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የትራምፕን ውሳኔ በመቀልበስ አሜሪካን ወደ የዓለም ጤና ድርጅት አባልነት መልሰዋል። አሜሪካ ለድርጅቱ የምታደርገው ከፍተኛ ድጋፍም ቀጥሏል።
በውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፉት ዶ/ር ቴድሮስ ግዙፉን የጤና ድርጅት ለሌላ አምስት ዓመታት የመምራት ጽኑ ፍላጎት አላቸው ተብሏል።