አውስትራሊያ የታዋቂውን የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪችን ቪዛ ዳግም ሰረዘች

ኖቫክ ጆኮቪች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

አውስራሊያ ዳግም የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጆኮቪች ቪዛን ሰረዘች።

ጆኮቪች የኮቪድ ክትባት ባለመውሰዱ በአውስራሊያ የመቆየት መብቱ ተሰርዟል።

የአውስትራሊያ መንግሥት ይህ ውሳኔ ያስተላለፈው "ጤና እና መልካም ሥርዓት" በሚል መመሪያ መሠረት ሲሆን፤ በዚህም ጆኮቪች ከአውስራሊያ ሊባራር እና የሦስት ዓመት የቪዛ እገዳ ሊጣልበት እንደሚችል ተመልክቷል።

ይሁን እንጂ 34 ዓመቱ ሰርቢያዊ ዳግም በአውስትራሊያ ለመቆየት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ይችላል።

ከሳምንት በፊት የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ኖቫክ ጆኮቪች ወደ አውስትራሊያ ሊገባ ያደረገው መኩራ ሜልበርን ከደረሰ በኋላ በተፈጠረ ግርግር በኢሚግሬሽን ማዕከል ውስጥ ለመቆየት ተገዶ ነው።

ጆኮቪች በወቅቱ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የሚስችለውን ቅደመ ሁኔታ አሏማላም ተብሎ ወደመጣበት እንዲመለስ ታዞ ነበር። ይሁን እንጂ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ከተከራከረ በኋላ በአውስትራሊያ እንዲቆይ ተፈቅዶለት ነበር።

ለውድድር ወደ ስፍራ የተጓዘው ጆኮቪች፤ ሰኞ በሚጀመርው የአውስራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ቀጠሮ ይዟል።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የጆኮቪች ቪዛ ዳግም የተሰረዘው "ጥንቃቄ በተሞላበት ውሳኔ" መሆኑን ተናግረዋል።

በአውስትራሊያ ሕግ መሠረት የተለየ የጤና ፍቃድ እስካልተገኘ ድረስ የተሟላ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ያልወሰደ ሰው ወደ አገሪቱ መግባት አይችልም።

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ዜጎች ዝነኛ፣ ባለጸጋ የሆኑ እና ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል ሲሉ መንግሥታቸውን ያብጠለጥላሉ።

የኮቪድ ክትባት ያልወሰደው ጆኮቪች ቅዳሜ ጠዋት ላይ ከአውስትራሊያ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ጋር በሜልበርን እንደሚገናኝ ተገልጿል።

ጆኮቪች ከሳምንት በፊት ወደ አውስትራሊያ አትገባም በተባለ ጊዜ ጠበቆቹን አቁሞ ተከራክሮ ነበር። የጆኮቪች የጠበቆች ቡድን እንደሚለው በቅርቡ በቫይረሱ መያዙ በቂ የሆነ የጤና ፈቃድ ያስገኝለታል በማለት ተከራክረው ቪዛ እንዲሰጠው አድርገው ነበር።

ዘጠኝ ጊዜ የአውስትራሊያ ኦፕን ውድድርን ያሸነፈው ጆኮቪች በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደውን ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆኖ የሚያሸነፍ ከሆነ፤ ስኬታማው የቴኒስ ተጫዋች ይሆናል።