በኮቪድ የተያዘ ልጇን ኮፈን ውስጥ ቆልፋበታለች የተባለችው አስተማሪ ታሰረች

በሎስ አንጀለስ የኮቪድ-19 መመርመሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካዊቷ አስተማሪ ኮቪድ የተያዘ ልጇ ቫይረሱ እንዳያስተላልፋበት በማለት የመኪናዋ ኮፈን ውስጥ ቆልፋበታለች ተብላ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ተዘግቧል።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ልጇ ተመርምሮ ውጤቱን ካወቀ በኋላ ነው ኮፈን ውስጥ አስገብታ እየነዳች የሄደችው።

የ41 ዓመቷ ሳራህ ቢም የሕፃናትን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል ተከሳለች።

በፈንጆቹ ጥር 3 አንድ የዓይን ምስክር ከአስተማሪዋ መኪና ኮፈን ውስጥ ድምፅ ሰምቶ ለፖሊስ በመጠቆሙ ነው ግለሰቧ በቁጥጥር ሥር የዋለችው።

ተጠርጣሪዋ ይህንን የፈፀመችው ቴክሳስ ውስጥ በምትገኘው ሃሪስ ክፍለ ግዛት ውስጥ ነው።

ፖሊስ ከደረሰ በኋላ የአስተማሪዋ ኮፈን ሲከፈት ልጇ ተንጋሎ ተገኝቷል ሲሉ መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበዋል።

አስተማሪዋ የ13 ዓመት ልጇ ኮቪድ ፖዘቲቭ በመሆኑ ወደ ሌላ ሕክምና ጣቢያ ወስዳ ውጤቱን ልታረጋግጥ እየወሰደችው እንደሆነ ተናግራለች።

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ሴትዬዋ ይህንን ድርጊት የፈፀመችው ልጇ ኮቪድ እንዳያስተላልፋባት በመስጋት ነው።

አንድ የጤና ባለሙያ ልጇ ከኮፈን ውስጥ ወጥቶ መኪናው ውስጥ እስካልተቀመጠ ድረስ የኮቪድ ምርመራ አላደርግም ማለቱም ተዘግቧል።

ግለሰቧ ሳይፕረስ ፎልስ ሃይ ስኩል የተሰኘ ትምህርት ቤት አስተማሪ ብትሆንም አሁን ግን በግዴታ እረፍት እንደትወስድ ተደርጓል።

ላለፉት 11 ዓመታት በዚህ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ያገለገልችው ቢም በቁጥጥር ሥር ውላ ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።

"እንደ ዕድል ሆኖ ሕፃኑ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም" ሲል የአካባቢው ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።