ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፕል ኩባንያ የገበያ ዋጋ ተመን ሶስት ትሪሊዮን ዶላር ደረሰ
አፕል የቴክኖሎጂ ኩባንያ ክብረ ወሰን ሰብሯል፡፡
በዓለም ላይ የኩባንያው ዋጋ ግምት እስከዛሬ 3 ትሪሊዮን የደረሰ አንድም ኩባንያ የለም፡፡ አፕል ይህን አሳክቷል፡፡
የኩባንያው የገበያ ግምት ዋጋ (market valuation) ማለት አንድ ኩባንያ የድርሻ ገበያ ላይ ሊያወጣ የሚችለው ሃብት ተሰልቶ የሚቀርብ ጥቅል የኩባንያ የሃብት ተመን ነው፡፡
ሟቹ ስቲቭ ጆብስ እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ በ2007 የመጀመርያውን አይፎን ስልክ ካስተዋወቀ ጀምሮ የኩባንያው የድርሻ ዋጋ በ5,800% ሲመነደግ ነበር፡፡
ይህ የኮቪድ ተህዋሲ ወረርሽኝ ለአፕል ሰርግና ምላሽ ሆኖለት ሰንብቷል ይላሉ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ተንታኞች፡፡
በርካታ ሰዎች ቤት ውስጥ ታጥረው እንዲቀመጡ በሆኑባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ የአፕል ምርቶችን ሸምተዋል፡፡
አፕል ስማርት ስልኮችን፣ ላፕቶፕና ታብሌቶችን እንደዚህ ጊዜ ገበያ ቸብችቦ አያውቅም ነው የተባለው፡፡
የአፕል ኩባንያ የገበያ ግምት ከ2 ትሪሊዮን ዶላር ወደ 3 ትሪሊዮን ዶላር ለማሻቀብ 16 ወራት ብቻ ናቸው የወሰዱበት፡፡
በሐምሌ 2017 ይኸው ኩባንያ ግምቱ 1 ትሪሊዮን ደርሶ የዓለም ዜና ሆኖ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ለአፕል ከፍተኛ ሽያጭ ካሉት ሸቀጦች እንደ ስማርት ስልኮቹ የሚሆንለት የለም.
የሽያጭ መዝገቡ እንደሚያሳየው ከዓመታዊ ሽያጩ ከታብሌቶችም ሆኑ ከማክ ላፕቶቹ በላይ የጠቅላላ ሽያጩን ግማሹን ድርሻ የሚይዘው ተወዳጆቹ አይፎን ስልኮች ናቸው፡፡
ሌላው የአፕል አዲሱ ገበያ እየሆነለት ያለው በአፕል ስቶር የሚሸጡ መተግበሪያዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ በአይ ክላውድ የዳታ የመጋዘን ኪራይ በመሰብሰብም ከባድ ትርፍ ያጋብሳል፡፡
ባለፈው ነሐሴ ከስቲቭ ጆብስ የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን የተረከቡት የዚህ ቁጥር አንድ ግዙፍ ኩባንያ ኃላፊ ቲም ኩክ 10 ዓመት ደፍነዋል፡፡
ሲቀጠሩ በተገባላቸው ቃል መሠረትም ኩባንያውን ከማንም በላይ ስላደረጉት፣ ተወዳዳሪዎቻቸውንም በብዙ ርቀት ጥለው በመሄዳቸው የ5 ሚሊዮን ሼር ተበርክቶላቸዋል፡፡
በአፕል የአንድ ሼር ዋጋ 750 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡
መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገው ይህ የዓለም ግዙፉና አትራፊው ኩባንያ አፕል የተመሠረተው እንደ ፈረንጆቹ በ1976 ሲሆን መሥራቾቹ ስቲቭ ጆብስና ሸሪኮቹ፣ ማለትም ሮናልድ ዋይኒ እና ስቲቭ ዎዝኒያክ ነበሩ፡፡