ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ላይ በድጋሜ እሳት ተነሳ
ኬፕታውን በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ የእንደራሴዎች ምክር ቤት የደረሰው ከባድ የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ውሏል ከተባለ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በድጋሜ ተቀስቅሷል።
ሰኞ እለት ከህንጻው ጣሪያ ላይ ነበልባል የታየ ሲሆን የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለማጥፋት ሲረባበረቡ ታይተዋል።
እሁድ በተቀሰቀሰው መጀመሪያው እሳት አደጋ የብሔራዊ ምክር ቤቱን ወይም የታችኛውን ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሟል።
ፖሊስ በቃጠሎ፣ ቤት በመስበር እና በስርቆት የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ማክሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
ባለሥልጣናት በህንጻው ምንጣፎች እና የእንጨት ወለሎች ምክንያት የእሳት ቃጠሎ ሊባባስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የፓርላማው ቃል አቀባይ ሞሎቶ ማታፖ ለደቡብ አፍሪካው ታይምስላይቭ እንደተናገሩት የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለመከላከል "ሌሊቱን ሙሉ ሠርተዋል።"
ሰኞ የተከሰተውን እሳት ለመከላከል 12 የእሳት አደጋ ተከላካዮች በቦታው ላይ ነበሩ ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ተጨማሪ ባለሙያዎች ቢላኩም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የእሳት ነበልባል ከህንጻው ሲወጣ ይታይ ነበር።
ከከተማው ማዘጋጃ ቤት በተሰጠው ተጨማሪ መረጃ መሠረት የሕንፃው አራተኛ እና አምስተኛ ፎቅ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። እሳቱ ስለመጥፋቱ እስካሁን አልታወቀም ።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እሑድ እሳት ሲከሰት ውሃ የሚረጨው የህንጻው መሣሪያ በትክክል እንዳልሠራ ተናግረዋል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች በደቂቃዎች ውስጥ "ለአስፈሪው እና ለአውዳሚው ክስተት" ለሰጡት ምላሽ አወድሰዋቸዋል።
የመንግስት ሚኒስትር ፓትሪሺያ ዴ ሊል በበኩላቸው የመጀመርያው ቃጠሎ ሲነሳ ደህንነት ካሜራዎች ላይ ትኩረት አለመደረጉን ገልጸው ነበር።
የእሑዱ እሳት የብሔራዊ ምክር ቤት ምክር ቤቱ "ሙሉ በሙሉ እንዲቃጠል" ምክንያት ሆኗል ብለዋል። ከአውሮፓውያኑ1884 ጀምሮ አገልግሎት ሲሰቱ ነበሩ የፓርላማው ክፍሎችም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ፓርላማው በበዓል ምክንያት ሥራ ላይ ባለመሆኑ የተጎዳም የለም።
ህንጻው በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርሶችን ጨምሮ ታሪካዊ መጽሐፎችን፣ ፎቶዎችን እና የጥበብ ሥራዎችን የያዘ ሲሆን ከእሳት ማትረፍ መቻሉን ባለስልጣናት ተናገዋል።
120 ሜትር ርዝመት ያለው እና የደቡብ አፍሪካን ታሪክ የሚመዘግብው የኬይስካማ ታፔስትሪ ተጎድቷል ወይም ወድሟል የሚል ስጋት ነበር።
በኬፕታውን ያሉት ምክር ቤቶች በሦስት ክፍሎች የተዋቀሩ ሲሆን ጥንታዊው በአውሮፓውያኑ 1884 የተገነባ ነው ነው። በ1920ዎቹ እና 1980ዎቹ የተገነቡት አዳዲሶቹ ክፍሎች ብሔራዊ ምክር ቤቱን ይይዛሉ። የሃገሪቱ መንግስት መቀመጫውን በፕሪቶሪያ አድርጓል።
ራማፎሳ እሑድ "በዲሞክራሲ ቤቱ ላይ በደረሰው ውድመት" ማዘናቸውን ተናግረው ነበር።
ፓርላማው በስራው ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም አይነት መስተጓጎል ለመቀነስ "ሁሉም ጥረቶች" እንደሚደረግ ተናግሯል። ሕንፃው በድጋሚ ለመጠቀም ብዙ ወራት ሊጠይቅ እንደሚችል ይገመታል።
የኬፕታውን ከንቲባ ጆርዲን ሂል-ሌዊስ የከተማው ምክር ቤት ለፓርላማው መሰብሰቢያ አማራጭ ሆኖ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።
ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፓርላማው ላይ የተከሰተ ሁለተኛው የእሳት አደጋ ነው። በመጋቢት ወር በኤሌክትሪክ ምክንያት የእሳት ቃጠሎ ደርሶ ነበር።
ባለፈው ዓመት በተነሳ የሰደድ እሳት የአፍሪካ መዛግብት የሚገኝበትን የኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ቤተመጽሐፍት ወድሟል።