በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ በሕንድ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

የህክምና ባለሙያዎች ሕክምና ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በሦስተኛ የኮሮናቫይረስ ማዕበልን ውስጥ የምትገኘው ሕንድ በዋና ከተማዋ ኒው ዴሊሂ እንዲሁም በፋይናንስ ማዕከልዋ ሙምባይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

ትላንት ማክሰኞ በአገሪቱ 37 ሺህ 379 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በሳምንት ውስጥ የአምስት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። ባለሙያዎች የመጨመሩ ምክንያት ኦሚክሮን የተባለው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ነው ብለዋል።

በቫይረሱ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የሚሆኑት በዴሊሂ እና ሙምባይ የሚኖሩ ሲሆን ይህም በከተሞቹ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሆነ አመላካች ተደርጓል።

በዚህም ሳቢያ የሁለቱ ከተሞች አስተዳደር የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሰዓት እላፊ ገደብን ጨምሮ ሌሎች ገደቦችን ይፋ አድርገዋል።

የሕንድ የክትባት ግብረ ኃይል ኃላፊ ዶ/ር ኤንኬ አሮራ ሦስተኛው የወረርሽኙ ማዕበል በአገሪቱ መጀመሩን ገልፀው "ሙሉው ማዕበሉ በአዲሱ ዝርያ... ኦሚክሮን ምክንያት የመጣ ይመስላል" ሲሉ ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

አገሪቱ እስካሁን ከ1 ሺህ 700 በላይ በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎችን ሪፖርት አድርጋለች።

ከዚህ መካከል ዋና ከተማዋ ሙምባይ 568 ሰው በመመዝገብ ከፍተኛ ቁጥር የያዘች ሲሆን ዴልሂ 382 ሰዎች በመመዝገብ ሁለተኛ ላይ ተቀምጣለች።

የዴልሂ የጤና መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሳትየንዳር ጃይን በከተማው ውስጥ 81 በመቶው የኮቪድ ምርመራዎች በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎችን እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል።

በዴልሂ የሚገኘው እና ከሕንድ ዋና ዋና ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው የመላው ሕንድ የህክምና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የተሰኘው ሆስፒታል ለዶክተሮች የክረምት ፈቃድ የመስጠት ተግባሩን መሰረዙ ተዘግቧል።

እየጨመረ የመጣው በቫይረስ የመያዝ ምጣኔ ሕንድ በሚያዝያ እና በግንቦት ወር ያጋጠማትን አስከፊ ሁለተኛ ማዕበል የሚያስታውስ ነው የተባለ ነው። በዚያ ወቅት ማዕበሉ የመጨረሻ ጫፍ ሲደርስ በየቀኑ በአማካይ ወደ 400,000 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ይያዙ ነበር።

በመላ አገሪቱ ያሉ ሆስፒታሎች የአልጋ እና ህይወት አድን ኦክሲጅን እጥረት የገጠማቸው ሲሆን በክፍት ቦታዎች ላይ የጅምላ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ለማከናወን አስገደዷቸው ነበር።

ያ ሁኔታ ቀንሶ ለበርካታ ወራት በቀን ከ10,000 በታች የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ነበር። ሆኖም አሁን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እንደገና ሲያሻቅብ የግዛት መንግሥታት እገዳዎችን መጣል ጀምረዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እንደሚያመለክተው በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎች ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ሲነጻፀር የሆስፒታል ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዝቅተኛ ናቸው፤ ነገር ግን በቫይረሱ የመያዝ መጠን መጨመር ሆስፒታሎች ላይ ጫና ስለሚፈጥር ባለሙያዎች ጥንቃቄ ማድረግን ይመክራሉ።

ትላንት ማክሰኞ በዴልሂ ከተማ ባለሥልጣናት በእረፍት ቀናት የሚደረጉ ሁሉንም ወሳኝ ያልሆኑ ተግባራት የሚከለክል ገደብ አውጥተዋል። ዋና ከተማዋ ባለፈው ሳምንት የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና ሲኒማ ቤቶች እንዲዘጉ እንዲሁም የምሽት የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች።

የእረፍት ቀናት ወይም የሳምንት መጨረሻ ላይ የሚተገበረው የሰዓት እላፊ ገደብ የታወጀው የከተማው ዋና አስተዳዳሪ አርቪንድ ኬጅሪዋል ቫይረሱ ከተገኘባቸው ከሰዓታት በኋላ ነው።

በሕንድ ውስጥ ከአዋቂዎች 63 በመቶ ያህሉ ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሲሆን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቢያንስ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደዋል።

ሕንድ እስካሁን ከ34 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 482 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን ሪፖርት አድርጋለች። ባለሙያዎች ግን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።