በህክምና ባለሙያዎች ታግዞ ራስን ማጥፋት የሚፈቅደው አዲስ ህግ በኦስትሪያ ተግባራዊ ሆነ

እጃቸው የተያያዙ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በህክምና ባለሙያዎች የታገዘ ራስን ማጥፋት የሚፈቅድ ህግ በኦስትሪያ ተግባራዊ ሆኗል።

ከያዝነው ቅዳሜ ጀምሮ፣ በጠና የታመሙ ወይም ቋሚና የማይሽር ህመም ያላቸው የኦስትሪያ አዋቂዎች የታገዘ ሞትን መምረጥ ይችላሉ።

በጉዳዩ ላይ የህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ የኦስትሪያ ፓርላማ አዲሱን ህግ በታህሳስ ወር አጽድቆታል።

ሆኖም ድርጊቱ ተግባራዊ ሲሆን ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታልም ተብሏል እያንዳንዱ ሞትም በሁለት ዶክተሮች ይገመገማል።

ከመካከላቸው አንዱም የማይድን በሽታን የሚያክሙና የህመምተኞችን የመጨረሻ ቀናት የተሻለ ለማድረግ የሚጥሩ የህክምና ባለሙያ መሆን አለበት።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ሌሎች አማራጮች ባሉበት ሁኔታ ማንም ሰው መሞትን እንዳይመርጥ ለማድረግም የማይድን በሽታን ህክምናን ለማዳበርና የህመምተኞችን የመጨረሻ ቀናት መቆያም ለማሻሻል መንግሥት ገንዘብ መመደቡን ተናግረዋል።

አንድ ሰው የራሱን ሕይወት እንዲያጠፋ መንገድ የሚመቻችበት ሁኔታ በጎረቤት ስዊዘርላንድ ሕጋዊ ነው።

በስፔን፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትም ከወንጀልነት እንዳይካተት ውሳኔ ተላልፏል።

ራስን ሆን ብሎ ለማጥፋት እርዳታን መጠየቅ በኦስትሪያ ህገ ወጥ እንደሆነ ይቆያል የተባለ ሲሆን አዲሶቹ ህጎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ወይም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸውን አያካትትም።

ራሳቸውን ለማጥፋት የሚፈልጉ አዋቂዎች ምርመራ ያደረጉበትን ማስረጃ እና የራሳቸውን ውሳኔ መፈጸም እንደሚችሉ ማረጋገጫ ሊኖራቸው ይገባል።

ከሁለት ዶክተሮች ፈቃድ ካገኙ በኋላ ታካሚዎች ውሳኔያቸውን ለማሰላሰል ለ 12 ሳምንታት መጠበቅ አለባቸው - ወይም በማይድን ህመም የተጠቁ ከሆነ ደግሞ ሁለት ሳምንታት ሊጠብቁ እንደሚገባ ህጉ አስቀምጧል።

ከዚህ የጥበቃ ጊዜ በኋላ በውሳኔያቸው ከጸኑ ለጠበቃ ወይም ምስክር ካሳወቁ በኋላ ገዳይ መድሃኒቶችን በፋርማሲ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።

እነዚህን መድሃኒቶች አላግባብ መጠቀምን ለመከላከል እነዚህን መድሃኒቶች የሚሸጡ የመድኃኒቶች መደብር ስም የሚገለፀው ለጠበቆች እና ለምስክሮች ሲሆን ሁኔታውም በይፋ አይነገርም።

እስካሁን ድረስ በኦስትሪያ ህግ አንድ ሰው እራሱን እንዲያጠፋ ያደረገ ወይም የረዳ ማንኛውም ሰው እስከ አምስት አመት እስራት ይጠብቀው ነበር።

የታገዘ ሞት ላይ የተጣለው ፍፁም እገዳ "የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይጥሳል" ሲል ባለፈው አመት የፌዴራል ፍርድ ቤቱ ሽሮታል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የተቀመጡ መስፈርቶችን ሳያሟሉ ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ እርዳታ ያደረጉ ግድያ በሚል ተመሳሳይ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

አዲሱ ህግ በዚህ አመት በፓርላማ ከመጽደቁ በፊት አንዳንድ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ሞትን እየጠየቁ ላሉ እርዳታ ፈላጊዎች ላይ ብዙ መሰናክሎችን አስቀምጧል ሲሉ ተከራክረዋል።

ሌሎች ደግሞ የታካሚዎችን የውሳኔ አሰጣጥ አቅም ለመገምገም የስነ አእምሮ ህክምና በቂ አይደለም ሲሉ በጣም ጥቂት መሰፈርቶች ናቸው የተገበሩት ሲሉ ተከራክረዋል።