ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
70 ልጆችን በጉዲፈቻ ያሳደጉ የሩሲያ ቄስ በህጻናት ጥቃት የ21 ዓመት እስር ተፈረደባቸው
የሩሲያ ፍርድ ቤት 70 ህጻናትን በጉዲፈቻ ተቀብለዋል በተባሉ የቀድሞ የኦርቶዶክስ ቄስ ላይ በህጻናት ላይ ጥቃት በመፈፀም የ21 ዓመት እስር በየነ።
ኖኮላይ ስትሬምስኪ የተባሉት እኝህ ቄስ ፍርዱ የተላለፈባቸው በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ውስጥ ኡራል በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በርካታ ልጆችን በመድፈርና ሌሎች ጥቃቶችን በመፈፀም ነው።
ስትሬምስኪ በሩሲያ ባላቸው ትልቅ ቤተሰብ ስማቸው የሚነሳ ሲሆን በብሔራዊ ደረጃም የወላጅነት ክብርን የተጎናጸፉ ነበሩ።
አሁን ግን በፈፀሙት ድርጊት ከክህነታቸው ታግደው ክብራቸው ተነጥቋል።
በሳራክታሽ ከተማ የገዳማት ኃላፊ የነበሩት ስትሬሚስኪ እና ባለቤታቸው ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በአካባቢው የሚገኙ ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ህጻናትን በጉዲፈቻ ተቀብለው ያሳድጉ ነበር።
በጉዲፈቻ ካሳደጓቸው 70 ህጻናት መካከልም አብዛኞቹ አድገዋል፤ ትዳር የመሠረቱም አሉ።
የቀድሞ ቄሱ በአውሮፓውያኑ 2019 በቁጥጥር ሥር ውለው በሰባት ታዳጊዎች ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን እርሳቸው ግን ድርጊቱን እንዳልፈፀሙና የቀረበባቸው ክስ የስም ማጥፋት ነው ሲሉ አውግዘውታል።
ባለፈው ዓመትም በእርሳቸው እጅ ካደጉ ልጆች መካከል አንዷ እና ባለቤቷ ህጻናትን በሕገ ወጥ መንገድ ነጻነታቸውን በመገደብ በእርሳቸው ላይ ያቀረቡትን ክስ ተከትሎ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳይፈጽሙ የእገዳ ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር።
በመጨረሻም አርብ ዕለት በሳራክታሽ የሚገኘው ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባቸው በነበሩት ስትሬሚስኪ ላይ በጉልበት ሥራ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ እንዲነጠሉ በሚያደርገው የቅጣት ሕግ መሠረት ለ20 ዓመታት ያህል ከህጻናት ጋር እንዳይሰሩ አግዷቸዋል፤ የነበራቸውን የወላጅነት ክብርም ነጥቋቸዋል።