በሚየንማር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው የጅምላ ግድያ ሲገለጥ

የሚየንማር ጦር በሐምሌ ወር ብቻ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተከታታይ የጅምላ ግድያ የፈጸመ ሲሆን ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸውንም የቢቢሲ ምርመራ አረጋግጧል።
የዓይን እማኞች እና በህይወት የተረፉ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአስራ ሰባት ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ወታደሮቹ የአካባቢውን ሰዎች ከሰበሰቡ በኋላ ወንዶቹን ለይተው ገድለዋል።
አብዛኞቹ የተገደሉት ሰዎች መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ስቃይ እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ምስሎች የወጡ ሲሆን ከዚያም በኋላ ጥልቀት በሌለው መቃብር ተቀብረዋል።
ግድያው የተፈፀመው በሐምሌ ወር በአራት የተለያዩ አጋጣሚዎች ሲሆን ስፍራውም በማዕከላዊ ሚየንማር ውስጥ በሳጋንግ አውራጃ ውስጥ የተቃዋሚዎች ምሽግ በሆነችው በካኒ ከተማ ነው።
ግድያው በየካቲት ወር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ አስተዳደሩ ወደ ዲሞክራሲ ይመለስ በሚሉ የሚሊሺያ ቡድኖች በጦሩ ላይ ለፈጸሙት ጥቃት አፀፋዊ ቅጣት ነው ተብሎ ይታሰባል። የወታደራዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ውንጀላውን አልካዱም።
ጦሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን በአንግ ሳን ሱሲ የሚመራውን መንግሥት በኃይል አስወግዶ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሲቪሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ቢቢሲ በካኒ ከተማ 11 የዓይን እማኞችንና ምስክሮችን አናግሮ ቃላቸውን መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ካደረገው ሚየንማር ዊትነስ በሞባይል ስልክ ከቀረጻቸው ቪዲዮዎችና ፎቶዎች ጋር አመሳክሯል።
ሚየንማር ዊትነስ በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያጣራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
ከፍተኛ ግድያ የተፈጸመው በይን መንደር ቢያንስ ሲሆን በዚህም 14 ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተሰቃይተው ወይም በድብደባ የሞቱ ሲሆን አስከሬናቸውም በደን በተሸፈነ ሸለቆ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።
ማንነታቸውን ለመጠበቅ ቢቢሲ ስማቸውን የማይገልጸው በይን የሚገኙ ምስክሮች እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ከመገደላቸው በፊት በገመድ ተጠፍረው ታስረው እንደነበርና እንደተደደቡም ገልጸዋል።
"ግድያውን ለማየት ስላልቻልን አንገታችንን ደፍተን እያለቀስን ነበር" በማለት ወንድሟ፣ የወንድሟ ልጅ እና አማችዋ የተገደሉባት አንዲት ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"እንዳይገድሏቸው ተማጸንናቸው። ምንም ግድ አልሰጣቸውም። በአካባቢውን የነበርነውም ሴቶች 'ባሎቻችሁ ከነዚህ መካከል አሉ ወይ?' ብለው ጠየቁንና ካሉ የመጨረሻ ስንብታችሁን አድርጉ" አሉን ብላለች።
ከግድያው ማምለጥ የቻለ አንድ ግለሰብ በበኩሉ ወታደሮቹ ከመግደላቸው በፊት ለሰዓታት ያህል ዘግናኝ በደል ፈጽመውባቸዋል ብሏል።
"ታስረው በድንጋይና በጠመንጃ እየተደበደቡ ቀኑን ሙሉ ሲሰቃዩ ነበር" ሲል ተናግሯል።
"አንዳንድ ወታደሮች ታዳጊ ይመስላሉ፣ ምናልባት 17 ወይም 18። ነገር ግን አንዳንዶቹ በእርግጥ ያረጁ አሉ በተጨማሪም አንዲት ሴት ከእነርሱ ጋር ነበረች" ብሏል።

በአቅራቢያው በሚገኘው የዚ ቢን ዲዊን መንደር፣ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ 12 የተቆራረጡ አስከሬኖች ጥልቀት በሌላቸው የጅምላ መቃብሮች ውስጥ ተቀብረው ተገኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የህፃን የሚመስል ትንሽ አካል፣ አካል ጉዳተኛ አስከሬኖች ያሉበት ሲሆን አንዳንዶቹም ተቆራርጠዋል።
በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ የአንድ ግለሰብ አስከሬን በአቅራቢያው ካለ የሮማን ዛፍ ላይ ታስረው ተገኝቷል።
ቢቢሲ የገመገመው የግለሰቡ አስከሬን ቪዲዮ እንደሚያሳየው የስቃይና የእንግልት ምልክቶች እንዳሉበት ነው።
ቤተሰቦቻቸው እንደተናገሩት ወታደሮቹ ወደ መንገደሩ ሲገቡ ልጁ እና የልጅ ልጃቸው ሸሽተው ነበር ነገር ግን እሳቸው በእድሜ ጠና ያሉ ስለሆኑ ጉዳት ይደርስብኛል ብለው አልጠበቁም ነበር።
ግድያው በአካባቢው በሚገኙ ዲሞክራሲ እንዲመለስ የሚጠይቁ የሲቪል ሚሊሻ ቡድኖች በወታደራዊ ኃይሎች ላይ ባደረሱት ጥቃት አጻፋዊ ምላሽ (ቅጣት) እንደሆነም ተነግሯል።
የጅምላ ግድያ ከመደረጉ በፊት ባሉት ወራት ውስጥ በአካባቢው በሚገኘው የሲቪል ሚሊሻ ቡድኖች ወይም የሕዝብ መከላከያ ሠራዊትና በጦር ሠራዊቱ መካከል የቀጠለው ግጭት ተባብሶ ነበር።
ቢቢሲ ከሰበሰባቸው ምስላዊ ማስረጃ እና ምስክርነት መረዳት እንደሚቻለው ግድያው ወንዶችን ኢላማ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም በቅርብ ወራት ውስጥ በመላው ሚየንማር በሕዝብ መከላከያ ሠራዊት እና በወታደሩ መካከል በተፈጠረው ግጭት ወንድ የመንደር ነዋሪዎች የቅጣቱ ተቀባይ ሆነዋል ከሚሉ ሪፖርቶች ጋር ተመሳሳይ ነው።
የተገደሉት ቤተሰቦች ግለሰቦቹ በወታደሮች ላይ በተፈፀመ ጥቃት እጃቸው እንደሌለባቸው በፅናት ይከራከራሉ።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ የውጭ ጋዜጠኞች በሚየንማር እንዳይዘግቡ የተከለከሉ ሲሆን አብዛኞቹ የመንግሥት ያልሆኑ ሚዲያዎችም መዘጋታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነት ለመዘገብ ፈታኝ አድርጎታል።
ቢቢሲ ጅምላ ግድያዎቹን አስመልክቶ ለሚየንማር የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር እና የወታደራዊ ቃል አቀባይ ጄኔራል ዛው ሚን ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም ወታደሮቹ የጅምላ ግድያ መፈጸማቸውን አልሸሸጉም።
"ሊፈጠር ይችላል፤ እኛን እንደ ጠላት ሲያዩንና ሲያጠቁን ራሳችንን የመከላከል መብት አለን" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚየንማር ጦር ተፈጽሟል ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በማጣራት ላይ ነው።












