የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ጃኮብ ዙማ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ አዘዘ

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በህክምና ሰበብ የተለቀቁበት ምክንያት ህገወጥ ነው በማለት ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ወስኗል።

ከእስር ቤት ውጪ ያሳለፉት ጊዜም ከ15 ወራቱ የእስራት ጊዜ ውስጥ ተካቶ ሊቆጠር አይገባም ሲል የፕሪቶሪያ ፍርድ ቤት ወስኗል።

ዙማ እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 5፣ 2021 ላይ ባልተገለጸ የጤና ችግር ከእስር ቤት ወጥተዋል።

በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው በሙስና ላይ በተካሄደው ምርመራ ላይ ለመቅረብ አሻፈረኝ በማለታቸው ነበር እንዲታሰሩ የተፈረደባቸው።

የ79 አመቱ አዛውንት በሀምሌ ወር በተነሳ ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት እራሳቸውን ለፖሊስ አስረክበው እስራቸውን ጀምረው ነበር። ሆኖም እስራቸው ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ዘረፋ አስከትሏል።

ከ300 በላይ ሰዎች በተቃውሞው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በአብዛኛው ሟቾች ዙማ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው በሚነገርላት በኩዋዙሉ-ናታል ግዛት ነዋሪ ናቸው።

ዙማ እንዲቀርቡ በተጠየቁበት ምርመራው አንድ ጊዜ ብቻ የተገኙ ሲሆን "መንግስታዊ ብልሽት/ሙስና" እየተባለ የሚታወቀው ክስ አካል ነው። ክሱ የመንግስት ውሳኔዎች የንግድ ሰዎችን ፍኣጎት ለማሳካት ያልተጋባ ግንኙነት መስርቷል የሚለው ነው።

ዙማ እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ከነበረ የጦር መሳሪያ ውል ጋር በተያያዘም የሙስና እና የማጭበርበር ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሆኖም የቀድሞ ፕሬዝዳንት የፖለቲካ ሴራ ሰለባ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የእስር ቤቱ ባለስልጣናት ዙማ ከእስር የመፈታታቸው ሰበብ ህክምና እንደሆነ ቢገለጽም ህመሙ ግን በፍፁም አልተገለጸም ብለዋል።

እሳቸው ግን ከታሰሩ በኋላ ቀዶ ህክምና አድርገዋል።

የዙማ ቃል አቀባይ በወቅቱ እስሩ "የጤና ሁኔታቸውን ከማባባስ አንፃር ትልቅ ተፅእኖ ነበረው" ብለዋል።

ጠበቆቹም የደንበኛቸው መታመም አቅመ ቢስ አድርጎታል ሲሉ ተከራክረዋል።

የደቡብ አፍሪካ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ቀደም ብሎ ዙማን ከእስር ለመልቀቅ የተላለፈውን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን በአዲሱ ውሳኔ መደሰቱን አስታውቋል።

"ይህ ለህግ የበላይነት እና በህግ ፊት ያለው የእኩልነት መርህ ለማረጋገጥ ትልቅ ድል ነው" ሲሉ የፓርቲው መሪ ጆን ስቲን ሁይሰን ተናግረዋል.

በፕሪቶሪያ የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማረሚያ አገልግሎት ሃላፊ አርተር ፍሬዘር የዙማ አጋር የቀድሞ መሪውን በህክምና ይቅርታ እንዲፈቱ ያስተላለፉት ውሳኔ "የተገመገመ፣ ህገወጥ ነው የተባለ እና ችላ የተባለ ነው" ብለዋል።

የዙማ ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ በመቃወም ይግባኝ በማለታቸው ወደ እስር ቤት በፍጥነት እንደማይመለሱም ታውቋል።