የአውሮፓ ኅብረት የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲን ዩክሬንን እንዳይጠቀልሉ ሊያስጠነቅቅ ነው

ታትሟል

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ሩሲያ በፍጹም ዩክሬን ላይ ወረራ እንዳትፈጽም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ሊሰበሰቡ ነው፡፡

የኅብረቱ አባላት በዚህ ማስጠንቀቂያቸው ፑቲን እንዳሰቡት ወረራ ቢፈጽሙ አገራቸው ከባድ ዋጋ እንደምትከፍል በግልጽ ቋንቋ ይነገራቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ መልእክት በብራስልስ የአውሮፓ ካውንስል ስብሰባ ላይ ይስተጋባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ግን የወረራ ሐሳቡን አስተባብሏል፡፡

የምዕራቡ አገራት የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ሩሲያ ቢያንስ መቶ ሺህ የሚሆነውን ሠራዊቷን ወደ ዩክሬን ድንበር እያስጠጋች እንደሆነ መረጃ አለኝ ይላል፡፡

የዩክሬን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሞስኮ ጥቃቱን በፈረንጆች አዲስ ዓመት ለማድረግ ነው ያቀደችው ይላሉ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ አካል የሆነው የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን አለቃ ሩሲያ በድንበር ያለውን ውጥረት እንድታረግብ ጠይቀው ነበር፡፡

ኡርሱላ ቮን ዴ ሌየን እንዳሉት ሩሲያ ወረራ ከፈጸመች ተጨማሪ ማዕቀቦች ይጣሉባታል፡፡

የኮሚሽን አለቃ ጨምረው እንዳሉት ሩሲያ ይህን ማስጠንቀቂያ የመትሰማ ከሆነ የሚጣልባት ማዕቀብ እጅግ ብርቱ፣ የብርቱ ብርቱ ይሆናል ብለዋል፡፡

ብዙዎች እንደሚገምቱት ከማዕቀቦቹ መካከል ሩሲያ ወደ ጀርመን እየዘረጋቸው ያለችው ግዙፍ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ (ኖርድ ስትሪም2) እንዲቋረጥ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ ዝርጋታ ገና ተጠናቆ ሥራ ያልጀመረ ፕሮጀክት ነው፡፡

የኮሚሽነሯ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮለድሚር ዘለንስኪ ጋር በብራስልስ ተገናኝተው መምከራቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የዩክሬኑ መሪ ዘለንስኪ ማዕቀቦቹ ሩሲያ ላይ መጣል ካለባቸው ከወረራው በኋላ ሳይሆን ጊዜው አሁን ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሩሲያ በሕግ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት ከምዕራባዊያን ጋር እንዲኖር ትፈልጋለች፡፡ ይህም ኔቶ ወደ ድንበሯ እንዳይጠጋ የሚያደርግ ነው፡፡

ኔቶ በበኩሉ እንቅስቃሴዎቼ በመከላከል ላይ የተገደቡ ናቸው ይላል፡፡

ዩክሬን ከአውሮፓ ኅብረትና ከሩሲያ ድንበር ብትጋራም ሕዝቧ ጥብቅ የባሕልና ቋንቋ ቁርኝት ያለው ከሩሲያ ጋር ነው፡፡

እንደተፈራው ፑቲን ዩክሬንን ቢጠቀልሏት በማዕቀብ ሐሳባቸውን ማስለወጥ ይቻላል ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡