ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ከክረምት ኦሊምፒክ እራሳቸውን የሚያገሉ አገራት 'የእጃቸውን ያገኛሉ' ስትል አስጠነቀቀች
ቻይና ከምታስተናግደው የቤይጂንግ የክረምት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እራሳቸውን የሚያገሉ አገራት "ለሚፈጽሙት ስህተት ዋጋ ይከፍሏታል" ስትል አስጠንቅቃለች።
ቻይና ሰብአዊ መብት እየጣሰች ነው በማለት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያና ካናዳ የመንግሥት ተወካዮቻቸውን እንደማይልኩ ይፋ አድርገዋል።
ቻይና ዊጋ ሙስሊሞች ላይ ሰብአዊ ጥሰት ትፈፅማለች የሚል ወቀሳ ይሰነዝርባታል።
ቀጣዩን የክረምት ኦሊምፒክ የምታዘጋጀው ፈረንሳይ ግን ከአጋሮቿ በተለየ እስካሁን ተወካዮቿን እንደማትልክ አላሳወቀችም።
የዘንድሮው የክረምት ኦሊምፒክ በሚቀጥለው የካቲት ቤይጂንግ ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።
"አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና አውስትራሊያ የኦሊምፒክ ጨዋታውን እንደ ፖለቲካ መድረክ ተጠቅመውበታል" ሲሉ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ተናግረዋል።
የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ረቡዕ ዕለት ቤይጂንግ "ወትሮውንም ቢሆን 'በአንሳተፍም ፖለቲካ' የናወዙ የአሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞችን የመጋበዝ ዕቅድ የላትም" ብሏል።
በዲፕሎማሲ ምክንያት አልሳተፍም ስትል መጀመሪያ ድምጿን ያሰማችው አሜሪካ ስትሆን፤ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ዩናይትድ ኪንግደም ተከታትለው ተመሳሳይ ሐሳባቸውን አሰምተዋል።
ይህ የአገራቱ አቋም ግን አትሌቶችን በጨዋታው ከመሳተፍ አያግዳቸውም። ይህን እርምጃ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚደገፍ ብሎታል።
"የመንግሥት ተወካዮችን መላክ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። ኮሚቴው በዚህ ውሳኔ እጁን አያስገባም" ብለዋል የኮሚቴው ፕሬዝደንት ቶማስ ባህ።
ከክረምት ጨዋታዎች እራሳቸውን የሚያገሉ አገራትና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል።
አሜሪካ፤ ቻይና በዢያንዢያንግ ግዛት ያሉ የዊጋና ሌሎች አናሳ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለት ስትል ትከሳለች።
ቻይና የሚቀርቡባትን ሁሉንም የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶች የምታጣጥል ሲሆን፤ በዢያንዢያንግ ግዛት ያሉት የማቆያ ካምፖች የዊጋ ሙስሊሞችንና ሌሎችን "መልሶ ለማስተማር" የሚውሉ ናቸው ትላለች።
ሌላው ቻይና የምትወቀስበት ጉዳይ በሆንግ ኮንግ ባለው ሁኔታና በቅርቡ የቻይና ባለሥልጣንን በወሲባዊ ጥቃት ምክንያት ከተናገረች በኋላ ለሳምንታት ሳትታይ በቆየችው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቿ ፔንግ ሹዋይ ነው።
የሴቶች ቴኒስ ማኅበር ባለፈው ሳምንት ቻይና የሚደረጉ ሁሉም የቴኒስ ውድድሮች የፔንግ ሁኔታ እስኪታወቅ ድረስ እንዲቋረጡ አዟል።
ቻይና ከካናዳ ጋር ያላት ግንኙነት የቆረቆዘው የቻይናው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመታሠሩ ምክንያትና በምትኩ ቻይና ሁሉት ካናዳዊያንን በማገቷ ምክንያት ነው። ሦስቱም ግለሰቦች በያዝነው ዓመት መባቻ ተለቀዋል።
ሌላኛው የመንግሥት ተወካዮቼን አልክም ያለችው አገር ኒው ዚላንድ ስትሆን፤ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቢያሳስባትም ተወካዮቿን ከመላክ የተቆጠበችው በኮቪድ ምክንያት ነው።
እንደ ጃፓን ያሉ ጎረቤት አገራትም ከጨዋታዎቹ እራሳቸውን ያርቃሉ የሚል ግምት አለ። ጣልያን እሳተፋለሁ ስትል ፑቲን የቻይናን ግብዣ ተቀብለው በሥፍራው እንደሚገኙ አሳውቀዋል።