በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን የደሞዝ ልዩነት ለምን ማጥበብ አልተቻለም?

ታትሟል

የሥነ ጾታ ባለሙያዎች እና የሴቶች መብት ተሟጋቾች ከሚያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች አንዱ ሴቶች እና ወንዶች እኩል ክፍያ ያግኙ የሚለው ነው።

ሴቶች እና ወንዶች በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ተቀጥረው ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ደመወዝ የሚያገኙባቸው አገሮች ብዙ ናቸው።

ይህንን የክፍያ ልዩነት ለማስቀረት ትግሉ ቢቀጥልም ባለፉት 25 ዓመታት እምብዛም ለውጥ እንዳልታየ አንድ ጥናት አመልክቷል።

በእርግጥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ የክፍያ መጠን ልዩነቱን ማጥበብ ተችሏል።

ኢንስቲትዩት ፎር ፊስካል ስተዲስ (አይኤፍኤስ) የተባለ የጥናት ተቋም እንደሚለው፤ ዝቅተኛው የደመወዝ መጠን ከፍ ማለቱ አነስተኛ ክፍያ የሚያገኙት ሰዎች ገቢ እንዲጨምር አግዟል።

ሆኖም ግን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ሰዎችን የክፍያ ልዩነት እምብዛም ማሻሻል አልተቻለም።

ትምህርት የክፍያ ልዩነትን አጥብቧል?

ዩናይትድ ኪንግደምን (ዩኬ) እንደ ማሳያ ወስዶ፤ በአይኤፍኤስ የተሠራው ጥናት የክፍያ ልዩነትን የመዘነው በሦስት መለኪያዎች ነው። የሥራ ቅጥር፣ የሥራ ሰዓት እና የደሞዝ መጠን።

ሴት ሠራተኞች በአንድ ወር ውስጥ ከወንድ ሠራተኞች በበለጠ ለ50 ሰዓታት እንደሚሠሩ ጥናቱ ደርሶበታል። ሴቶቹ እናቶች ከሆኑ በኋላ የክፍያ ልዩነት እና የሥራ ሰዓት ልዩነትም የበለጠ እየሰፋ ይሄዳል።

የክፍያ ልዩነት እምብዛም ባይጠብም፤ በመጠኑም ቢሆን ለውጥ እየታየ የመጣው ብዙ ሴቶች መማር ከመጀመራቸው ጋር በተያያዘ ነው።

እአአ በ2019 ዩኬ ውስጥ ሴት ሠራተኛ ከወንድ ሠራተኛ 40 በመቶ ያነሰ ገቢ ነበር የምታገኘው።

ይህ በ1990ዎቹ ከነበረው የደመወዝ ልዩነት የተሻለ መሆኑ አይካድም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለሴቶች የትምህርት ዕድል ክፍት መሆኑ ነው።

ከ25 ዓመታት በፊት አንዲት ሴት ሠራተኛ የዩኒቨርስቲ ዲግሪ የማግኘት ዕድሏ ከወንዶች አንጻር ጠባብ ነበር። ዛሬ ላይ ግን ለውጥ አለ።

በጥናቱ የተሳተፈችው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አሊሰን አንድሪው እንደምትለው፤ ትምህርት የክፍያ ልዩነትን በማጥበብ ረገድ አስተዋጽኦ አለው።

የፖሊሲ ክፍተቶች

በሴቶች እና ወንዶች መካከል እኩል የሥራ ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል በየጊዜው የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቢደረጉም በቂ እንዳልሆኑ አጥኚዎቹ ይገልጻሉ።

ጥናቱ ፖሊሲዎችን የሚገልጻቸው "ደካማ" እንዲሁም "ባህላዊ የጾታ ሚናን የሚከተሉ" በማለት ነው።

ሴቶች ኃላፊነታቸው "ልጅ ማሳደግ ነው" የሚለው የተዛባ የአባታዊ ሥርዓት ምልከታ ማኅበረሰቡን ወደኋላ እንደሚጎትትም ያክላሉ።

በለንደን የምጣኔ ሀብት ትምህርት ቤት የምታስተምረው ዶ/ር ግሬስ ሎርዳን እንደምትለው፤ የክፍያ ልዩነት በዓመታት አለመለወጡ አያስደንቅም።

"ሴቶች እና ወንዶች አንድ ዓይነት ዲግሪ ቢኖራቸውም እንኳን ሴቶች የሚከፈላቸው ከወንዶች ያነሰ ነው። መንግሥት ይህንን ለማስተካከል ተቋማት የአሠራር ማሻሻያ እንዲያደርጉ ጫና ማሳደር አለበት" ስትል ታስረዳለች።

ለዘመናት የተጠበቀው ለውጥ

የጥናቱ መሪ ሞኒካ ኮስታዲያዝ ሞኒካ እንደምትለው፤ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ እየተማሩ ቢሆንም ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት የክፍያ ልዩነት ያን ያህል መሻሻል አላሳየም።

"በሥራ ቅጥር፣ በሥራ ሰዓት እና በደመወዝ መጠን ያለው ልዩነት አልተለወጠም። ሴቶች የበለጠ እየተማሩ መምጣታቸው የክፍያ ልዩነትን ያጠባል ብለን መጠበቅም አንችልም" ትላለች።

ልጆች መንከባከብ እና የቤት ውስጥ ሥራን ጨምሮ ሌሎችም ያለ ክፍያ የሚሠሩ ሥራዎችን የሚይዙት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ናቸው።

ባለፉት 25 ዓመታት ሴቶች በክፍያ የሚሠሯቸው ሥራዎች ቢጨምሩም ያለ ክፍያ የሚሠሯቸው ሥራዎች አሁንም አልቀነሱም።

አጥኚዋ እንደምትለው፤ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሚይዙት ሥራ እኩል ክፍያ እንዲኖረው የሚያስገድዱ ፖሊሲዎች መውጣት አለባቸው።

የስዊዘርላንድ ተሞክሮ

አባቶች አዲስ ልጅ ሲወልዱ ከሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚደነግግ ሕግ አምና በስዊትዘርላንድ ጸድቋል። አላማውም የጾታ እኩልነትን ማስፈን ነው ተብሏል።

ለልጆች እንክብካቤ የሚወጣ ገንዘብ ከመመደብ አንስቶ እስከ የወሊድ ፈቃድ ድረስ የተሻለ ሕግ ያወጡ አገሮች የክፍያ ልዩነታቸው ጠባብ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል።

ዩኬ ውስጥ ሁለቱም ደመወዝተኛ የሆኑ ጥንዶች ከ20 በመቶ በላይ ገቢያቸውን የሚያውሉት ልጅ ለማሳደግ ነው።

በአገሪቱ ላለው የክፍያ ልዩነት ምክንያቶቹ ፖሊሲ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መርሆች እንደሆኑ ጥናቱ ይጠቁማል።

የወሊድ ፈቃድ የሚሰጠው ለሴቶች ከመሆኑም ባሻገር ልጆች ለመንከባከብ የሚወጣ ወጪም በሴቶች ጫንቃ ላይ ይወድቃል።

ይህ ደግሞ የክፍያ ልዩነትን ያሰፋል።

ዶ/ር ግሬስ ሎርዳን እንደምትለው የስዊትዘርላንድ ተሞክሮ የክፍያ ልዩነትን ለማጥበብ መነሻ ይሆናል።

ሴቶች እና ወንዶች የወሊድ ፈቃድ ሲያገኙ ማኅበራዊ አመለካከትን ከመለወጡ በተጨማሪ ከወጪ አንጻርም የሚደግፍ አካሄድ ነው።

በሴቶች እና ወንዶች መካከል የሚሰጠው የጾታ ሚና ከሚያገኙት ገቢ ጋር አይገናኝም።

ለምሳሌ ከባለቤቷ የበለጠ ገቢ የምታገኝ ሴት ስትወልድ የሥራ ሰዓቷን ትቀንሳለች።

በሌላ በኩል ሴቶች የትርፍ ጊዜ ሥራ ሲሠሩ የሚያገኙት ገንዘብ ውስን ነው። ለሙያዊ እድገታቸውም አያግዝም።

የክፍያ ልዩነት በሴቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አጉልቶ የሚያሳየው ያለ አጋር ልጅ የሚያሳድጉ ሴቶች ሕይወት ነው።

ክፍያ ያለው ሥራ ቢኖራቸውም እንኳን ለድህነት የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል።

ምን ይደረግ?

ይህ ጥናት የተሠራው ዩኬን መነሻ በማድረግ ቢሆንም ችግሩ ዓለም አቀፍ ነው።

በየአገሩ ያሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ለዘመናት ጥያቄያቸውን ማሰማትም ቀጥለዋል።

የጥናቱ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ የዩኬ መንግሥት የክፍያ ልዩነትን ለማሻሻል የሚጠበቅነትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቋል።

ምቹ የሥራ ሰዓት ማመቻቸት፣ የወሊድ ፈቃድን ለወንዶችም ለሴቶችም መስጠት፣ ለልጆች እንክብካቤ የሚውል ድጎማን መጨመር እና በሥራ ለሚወጠሩ ወላጆች ነጻ የልጆች ማቆያ ማዘጋጀት መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአገሪቱ መንግሥት እንደሚለው፤ የደመወዝ ልዩነት በአንጻራዊነት እየጠበበ መጥቷል። እአአ በ2010 ከነበረው አንጻር 1.9 ሚሊዮን ሴቶች ሥራ ይዘዋል።

"ፍትሐዊ አገር ለመገንባት ዝግጁ ነን። በሥራ ቦታ እኩልነት እንዲሰፍንም ቁርጠኛነታችንን እናረጋግጣለን" ሲልም በቃል አቀባዩ በኩል ገልጿል።