ኬንያዊው ፖለቲከኛ ለአዲስ ተጋቢዎች ብድር ለመስጠት ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከወራት በኋላ በሚደረገው የኬንያ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ፖለቲከኛ፤ ከተመረጡ ከ4,400 እስከ 8,800 ዶላር የሚደርስ ብድር ለአዲስ ተጋቢዎች ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንታዊ ማኒፌስቷቸውን እሑድ ይፋ ያደረጉት ማቻኮስ የተባለው ግዛት አገረ ገዢ አልፍሬድ ሙቱዋ፤ በ20 ዓመት የሚከፈልና ዝቅተኛ ወለድ ያለው ብድር ጥንዶች "ሕይወታቸው በክብር እንዲጀምሩ" ይረዳል ብለዋል።
"የዚህ ሁሉ ውጤት ምንድን ነው?" ብለው በመጠየቅ የጀመሩት ሙቱዋ "ለሁላችንም ክብር ነው። የኑሮ ደረጃን ከማሻሻል እና በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የመኖሪያ ቤቶችን ጥራት ከማሳደግ ባለፈ የጭቃ ቤቶችን ያስቀራል" ብለዋል።
ችግኝ ተከላ እንደ ጥሎሽ እንዲቆጠር መንግሥታቸው እንደሚያበረታታም ተናግረዋል።
በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ በተላለፈው የማኒፌስቶ ማስተዋወቂያ ዝግጅት ላይ "ጥሎሽ ለመክፈል ስትሄዱ ምን ያህል ዛፎች እንደተከላችሁ መናገር አለባችሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ የፖለቲከኛው ሃሳብ ግን ከሁሉም ዘንድ አውንታዊ ምላሽ አላገኘው፣ ከአንዳንድ የማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ተጠቃሚ ኬንያውያን በኩል የሰላ ትችት እና ፌዝ አስተናግዷል።
የ10 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው መገባደጃ ወራት ላይ የሚገኙትን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ለመተካት 10 የሚጠጉ ፖለቲከኞች በዕጩነት ለመቅረብ ከወዲሁ ዘመቻ ጀምረዋል።
ነሐሴ 2022 በሚካሄደው ምርጫ ዋና ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከተገመቱት አንጋፋው የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ እና የአሁኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ይገኙበታል።
ምጣኔ ሀብት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና ሙስናን መዋጋት የፕሬዝዳንትነቱን ቦታ በሚሹ ሰዎች ቁልፍ አጀንዳዎች ሆነው ብቅ ብለዋል።
ያለፉት ምርጫዎች የሚያሳዩት ግን ኬንያውያን ከፖሊሲ ጉዳዮች ይልቅ በጎሳ ወይም ሕብረት ፈጥረው ለሚመጡ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ታይቷል።












