ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማግዳሊና አንደርሰን፡ የስዊድን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣናቸው ተመለሱ
ባለፈው ሳምንት በፖለቲካ ውዥንብር በተሾሙ በሰዓታት ውስጥ ሥልጣናቸውን የለቀቁት የስዊድን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣናቸው ተመለሱ።
የፓርላማ አባላት ሰኞ ዕለት በሰጡት አዲስ ድምጽ የሶሻል ዲሞክራቲክ መሪ ማግዳሊና አንደርሰንን በጠባብ ልዩነት ደግፈዋል።
በዚህም መሠረት ማግዳሊና በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር እስከሚካሄደው ምርጫ ድረስ የአንድ ፓርቲ መንግሥት ይመራሉ ተብሏል።
ማግዳሊና ባለፈው ረቡዕ ዕለት ከርሳቸው ፓርቲ ጋር ጥምረት የፈጠረው የፖለቲካ ድርጅት ከጥምረቱ በመልቀቁና የሳቸው ፓርቲ ሶሻል ዲሞክራት ያቀረበው የበጀት ጥያቄ በምክር ቤቱ ሊያልፍ ባለመቻሉ ነበር ከተሰጣቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት የለቀቁት።
ማግዳሊና ሥልጣን ከመልቀቃቸው ከሰዓታት በፊት ነበር የስዊድን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በፓርላማው የተመረጡት።
ነገር ግን የ54 ዓመቷ ዓመቷ የምጣኔ ሐብት ምሁር ከግሪን ፓርቲ ጋር አዲስ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ይዘውት የነበረው እቅድ የበጀት ረቂቃቸው ባለመጽደቁ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ይልቁኑ ፓርላማው የቀኝ አክራሪዎቹን የስዊድን ዲሞክራቶችን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቡድን ያዘጋጁትን በጀት ተቀብሏል።
ግሪን ፓርቲ በቀኝ አክራሪዎቹ የረቀቀውን በጀት እንደማይቀበል ገልጿል።
ማግዳሊና በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል እንደማይፈልጉና የገዛ ፓርቲያቸው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግሥት ሲመሰርት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ሰኞ ዕለት በተካሄደው የስዊድን ፓርላማ ድምጽ አሰጣጥ ግን ሪክስዳግ የተባለው የስዊድን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 349 አባላቱ 101 የድጋፍ ፣ 75 ድምጸ ታቅቦ፣ 173 ደግሞ የተቃውሞ ደምጽ ሰጥተዋል።
በስዊድን የፖለቲካ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመሾም አንድ እጩ አብላጫ የተቃውሞ ደምጽን ማግኘት የለበትም።
ከድምጽ አጣጡ ሥርዓት በኋላ ማግሊንዳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በደህንነት ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በወንጀል ላይ ያተኮረ ፕሮግራም በመዘርጋት ስዊድንን ወደ ፊት ለማራመድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ነገር ግን አሁንም የሌሎች ፓርቲዎችን ድጋፍ ካላገኙ ሴንተር ሌፍት ሶሻል ዲሞክራቶች ከ349፣ 100 መቀመጫ ባላቸው ፓርላማ ሕግ ለማጽደቅ ይቸገራሉ ተብሏል።
ማግዳሊና በዩኒቨርስቲ ሲቲ ኡፕሳላ የአዳጊዎች የውሃ ዋና ሻምፒዮን የነበሩ ሲሆን ፖለቲካ ውስጥ የገቡት በ1996 የጠቅላይ ሚኒስትር ጎራን ፐርሰን አማካሪ በመሆን ነበር፡፡
ላለፉት ሰባት ዓመታትም በገንዘብ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
ማግደሊና አንደርሰን በሕዝብ እንደራሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ድምጽ ከማግኘታቸው በፊት ስዊድን ከኖርዲክ አገሮች ሁሉ ብቸኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ኖሯት የማያውቅ አገር ሆና ቆይታለች፡፡
ስዊድን የጾታ እኩልነት ከፍ ባለ ደረጃ የምታከብር አገር ናት፡፡